የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በአካባቢያዊና ማህበረሰባዊ ጉዳዮች ተፅዕኖ ግምገማ ጥናት ውጤት መሰረት መከናወኑን በፕሮጀክቱ የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያ አስታወቁ፡፡
ባለሙያው አቶ አዲሱ እጅጉ እንዳስታወቁት ፕሮጀክቱ በሚከናወንበት ወቅትና ወደ ኦፕሬሽን ሲገባ በአካባቢና በማህበረሰቡ ላይ ሊኖር የሚችለውን አሉታዊና አዎንታዊ ተፅእኖ ለመለየትና መፍትሔ ለማስቀመጥ የአካባቢያዊና ማህበረሰባዊ ጉዳዮች ተፅዕኖ ግምገማ ጥናት ተካሂዷል፡፡
ጥናቱ ፕሮጀክቱ በአካባቢው መልከዓ ምድር፣ በአየር ንብረት፣ በውሃ አካላት፣ በእፅዋት፣ በእንስሳትና ማህበረሰቡ ላይ ጉዳት ማድረሱንና አለማድረሱን ለማወቅ ትኩረት ያደረገ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡
በጥናቱ ላይ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት መሳተፋቸው እና ጥናቱ በትክክለኛመረጃ ላይ ተመስርቶ መከናወኑ ፕሮጀክቱ ወደ ትግበራ ሲገባ በማህበረሰቡ ተቀባይነት እንዲኖረው ከማድረግ ባለፈ ከማህበረሰቡ ለሚነሱ ጥያቄዎች በጥናቱ መሰረት ምላሽ መሰጠቱን ጠቅሰዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም መሬታቸው በፕሮጀክቱ ለተወሰደባቸው አካላት አስፈላጊውን የካሳ ክፍያ ለመፈፀም፣ ማህበረሰቡ በፕሮጀክቱ ላይ የባለቤትነት ስሜት እንዲኖረው እና ፕሮጀክቱን በተያዘለት ጊዜ እንዲከናወን ለማድረግ ማገዙንም አስረድተዋል፡፡
ፕሮጀክቱ አሁን ለደረሰበት አፈፃፀም የአካባቢያዊና ማህበረሰባዊ ጉዳዮች ተፅዕኖ ግምገማ ጥናት ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ባለሙያው አመልክተዋል፡፡
የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በአርሲ ዞን ሂጦሳ ወረዳ ከሚገኙ ቀበሌዎች አራቱን ያካልላል፡፡
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”


