በሀረሪ ክልል ሶፊ ወረዳ ሊገነባ የታሰበው ባለ 400 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት ብዙ ችግሮችን እንደሚፈታ እምነት እንዳላቸው በሶፊ ወረዳ የቃሊ ቀበሌ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡
የምሥራቃዊ ኤሌክትሪክ ግሪድ ማጠናከሪያ ፕሮጀክት አካል የሆነው ባለ 400 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት ግንባታ ለማስጀመር የሚያስችሉ ውይይቶች ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ተደርጓል፡፡
ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተውጣጡ የተወከሉ ባለሙያዎች ስለሚገነባው ፕሮጀክት ፋይዳ፣ ስለ ካሳ አከፋፈል ሁኔታ እና ፕሮጀክቱ ሲጀመር ለአካባቢው ማህበረሰብ ስለሚፈጥረው የሥራ ዕድል ለአካባቢው ነዋሪዎች አስረድተዋል፡፡
የሶፊ ወረዳ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊና የቃሊ ቀበሌ የልማት ተጠሪ አቶ አብዲ አወል እንደገለፁት የአካባቢው ነዋሪዎች የኤሌክትሪክ እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ጥያቄ ሲያነሱ ቆይተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ችግር ፈች የሆነ ትልቅ ፕሮጀክት ሊገነባ ማቀዱ ለአካባቢው ማህበረሰብና ለወረዳው ትልቅ ዕድል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ከተቋሙ ጋር በቅርበት ለመስራት ቁርጠኛ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል፡፡
የአካባቢው አርሶ አደር የሆኑት አቶ ቃሲም አብዱከሪም በበኩላቸው በአካባቢያቸው የሚገነባው ፕሮጀክት የንፁህ መጠጥ ውሃ እና የመብራት ችግሮችን እንደሚፈታላቸው ተስፋ ማድረጋቸውን ገልፀዋል፡፡
ሌላዋ የአካባቢው አርሶ አደር ወ/ሮ ሳሮ አሊይ በቀበሌዋ ምንም ዓይነት ውሃ ባለመኖሩ እስከ ስምንት ኪሎ ሜትር ተጉዞ ውኃ መቅዳት አሰልቺ የሴቶች የዘወትር ተግባር መሆኑን አንስተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ፕሮጀክቱን ሲገነባ ከኃይል አቅርቦት ጎን ለጎን ሌሎች ማህበራዊ ችግሮችን የሚፈታ በመሆኑ ግንባታው ሲጀመር እርሳቸውና ሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎች ለፕሮጀክቱ መሳለጥ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል፡፡
ከሀረር ከተማ በ15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሊገነባ የታቀደው ይህ ፕሮጀክት ከኤሌክትሪክ አቅርቦት ባሻገር ለአካባቢው ወጣቶች ቋሚና ጊዚያዊ የስራ ዕድል ይፈጥራል፡፡
“ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”


