የሀረር ቁጥር 4 ባለ 400 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክትን ለማስጀመር የሚያስችሉ የዝግጅት ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን የምስራቅ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ግሪድ ማጠናከሪያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡
የፕሮጀክት ጽ/ቤቱ የሳይት ተወካይ አቶ መኮንን ዓለሙ እንዳስታወቁት ፕሮጀክቱ በሚያርፍበት ቦታ ይዞታ ላላቸው አርሶ አደሮች ተገቢውን ካሳ ለመክፈል የእርሻ መሬት ልኬትና የተክል ቆጠራ ቀደም ብሎ ተከናውኗል፡፡
ይዞታቸው ለፕሮጀክቱ የሚፈለግ 40 የአካባቢው ነዋሪዎች በልኬቱና በቆጠራው መሠረት አስፈላጊውን ካሳ ከፍሎ ለግንባታ ዝግጁ ለማድረግ ከሚመለከታቸው የክልል፣ የወረዳና የአካባቢው መስተዳደሮች ጋር ሰፊ ውይይቶች መደረጋቸውን ተወካዩ አንስተዋል፡፡
ተቋሙ የቀረበለትን የካሳ ክፍያ መጠን አዋጁን መሠረት አድርጎ ለመክፈል ከተቋሙ የተውጣጡ የህግና የአካባቢ ጥናት ባለሞያዎች በስፍራው በመገኘት ክትትል ማድርጋቸውን ገልፀዋል፡፡
እንደ ተወካዩ ገለጻ ክልሉና ወረዳው ያዋቀሯቸው ኮሚቴዎች የካሳ ክፍያ ግምቱን አጠናቀው ለተቋሙ በአስቸኳይ እንዲያቀርቡ እና ወደ ሥራ እንዲገባ ከክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡
የማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክቱ በሚያርፍበት ቦታ ላይ ከፕላን ጋር ተያይዘው የተነሱ ጥያቄዎች መኖራቸውን ያነሱት ሥራ አስኪያጁ ጉዳዩ በክልሉ ምክር ቤት ታይቶ ውሳኔ እንዲሰጥ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በሀረሪ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ የከተማ ማደስና መልሶ ማልማት ቡድን መሪ አቶ ፈቲ ሁሴን በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በከተማዋና በዙሪያው ለሚገነቡ ኢንዱስትሪዎች አስተማማኝ ኃይል ለማቅረብ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ከመጀመሩ በፊት ለአርሶ አደሮቹ ተገቢውን ካሳ ለመክፈል ከክልሉና ከወረዳ መስተዳድር የተውጣጡ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ኮሚቴዎች ሲከታተሉ መቆየታቸውን አቶ ፈቲ አስታውሰዋል፡፡
የካሳ ክፍያ መመሪያው በሚያዘው መሠረት በየሁለት ዓመቱ የሚሻሻል መመሪያ መኖሩን የጠቆሙት አቶ ፈቲ በዚህ ምክንያት ግምቱ እንደዘገየ አስረድተዋል፡፡
አሁን ግን የካሳ ክፍያውን የመጨረሻ ግምት አፅድቆ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ ለአርሶ አደሮቹ ክፍያ የሚፈፀምበት የባንክ ደብተር፣ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ እና ተያያዥ ጉዳዮችን እየተጠናቀቁ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የሀረር ቁጥር 4 ባለ 400 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት ከሀረር ከተማ በ15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ቃሊ ቀበሌ ሊገነባ የታሰበ ፕሮጀክት ነው፡፡
ፕሮጀክቱ በአፍሪካ ልማት ባንክ ፋይናንስ የሚገነባ ሲሆን የምስራቅ ኢትዮጵያን የኤሌክትሪክ ግሪድ ለማጠናከር ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡
“ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”


