የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ወጥና በቴክኖሎጅ የታገዙ አሰራሮችን በመዘርጋት የኃይል መቆራረጥን ለማስቀረት እየሰራ መሆኑን በማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፊያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን ዘርፍ የቴክኒካል ድጋፍ መምሪያ አስታወቀ፡፡
የመምሪያው ዳይሬክተር አቶ አበባው ያለው እንደገለጹት በከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ የሚሰሩ የፍተሻና የጥገና ሥራዎችን በሁሉም ሪጅኖች ወጥነት ባለው መልኩ ማከናወን የሚያስችል አሰራር ተተግብሯል፡፡
የተበላሹ ዕቃዎችን፣ ማሻሻያ የሚፈልጉ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎችን በማጥናትና በመጠገን ከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችና የማከፋፊያ ጣቢያዎች ያለብልሽት በሙሉ አቅማቸው እንዲሰሩ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች እና የስርጭት መስመሮች ሲቆረጡ የተቆራረጡ መስመሮችን እና ያደረሱትን ጉዳት እንዲሁም ያልተሸጠ ኃይል የሚመዘግብ ኢኢፒ ሳውዝ ክላውድ የሚባል ሶፍትዌር በክፍሉ ሠራተኞች በልፅጎ ሥራ ላይ መዋሉንም ተናግረዋል፡፡
አር ቲ ኢ ኢንተርናሽናል ከሚባል የፈረንሳይ የትራንስሚሽን ካምፓኒ ጋር “ግሪድ ሞደርናይዜሽን” የሚባል ፕሮጀክት ተቀርጾ እየተሰራ ነው ያሉት አቶ አበባው ካምፓኒው እንዴት እየሰራ ነው የሚለውም ፈረንሳይ ድረስ በመሄድ የልምድ ልውውጥ ተደርጓል።
ካምፓኒው ፕላንት ሜንቴናንስ ለሚባለው የሳፕ ሞጁል የሚባል እስከ ሴሪያል ቁጥር ድረስ የወረደ የድርጅቱን ንብረት የሚመዘግብ አሰራር ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው ለዚህም ዳታ የማሰባሰብና የማደራጀት ሥራ ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው።
በተመሳሳይ ከኬኒያው አሞቴክ አፍሪካ ኩባንያ ጋር የትራንስፎርመርና ሌሎች ፍተሻዎችን ለማካሄድ ለመሃንዲሶች ስልጠና በመስጠት በጋራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ይህም የቴክኖሎጂና የዕውቀት ሽግግር እንዲኖር እድል በመስጠትና ሥራዎችን በማዘምን በኩል ሚናው የጎላ ነው ብለዋል።
መምሪያው ዳታ ቤዝ በማዘጋጀት በካምፓኒው ውስጥ ያሉ ዕቃዎችን እየመዘገበ እንደሚገኝ አስታውሰዋል።
አቶ አበባው እንዳሉት ሪጅኖች ያሉባቸውን የመለዋወጫ እጥረት በማጥናት ዋናው ፓወር ትራንስፎርመር አደጋ እንዳይደርስበት የሚከላከሉ 40 እርዚንግ ትራንስፎርመር እና 46 ሺ ሜትር የፓወር ኬብል ገመድ ግዥ ለመፈጸም ፕሮሰስ ተጀምሯል።
በዘርፉ ሥር የሚከናወኑ ሁሉንም ተግባራት የጥራት አስተዳደር ሥርዓት (QMS)ን የተከተለና የተቋሙን የ-ISO 9001 ዓለም ዓቀፍ ስታንዳርድ መርሆዎች የተከተለ እንዲሆን ሥርዓቶችን፣ ፕሮሲጀሮችን፣ ፖሊሲዎችን፣ ማኑዋሎችንም እያዘጋጀ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ተቋሙ ላሉት ለ13ቱ ሪጅኖች የሚሆኑ የሥራ ላይ ደህንነት ጨምሮ 7 ፕሮሲጀሮችንም አስጸድቆ ወደ ተግባር መግባቱን ገልጸዋል፡፡
“ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”