በክልሉ በሁለት ዓመት ተኩል ብቻ ከ76 ሚሊዮን ብር በላይ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ስርቆት ተፈጽሟል

በክልሉ በሁለት ዓመት ተኩል ብቻ ከ76 ሚሊዮን ብር በላይ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ስርቆት ተፈጽሟል

በኦሮሚያ ክልል በሁለት ዓመት ተኩል ብቻ 76 ነጥብ 07 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ስርቆት መፈጸሙን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ፡፡

ተቋሙ በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ስርቆት፤ በጸጥታ ሥጋቶች፣ በካሳ ክፍያ፣ በወሰን ማስከበርና ተያያዥ ጉዳዮች ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል መንግስት የሥራ ኃላፊዎች ጋር ምክክር አድርጓል፡፡

የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ የምክክሩን ዓላማ አስመልክተው እንደገለፁት በኃይል አቅርቦት ዘርፍ ተቋሙ እያከናወነ ያለውን ሰፊ የመሰረተ-ልማት ግንባታ እና የኦፕሬሽን ሥራዎች ለባለድርሻ አካላት በማስገንዘብ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ነው፡፡

የኤሌክትሪክ መሰረተልማት በሚገነባባቸውና በሚያልፍባቸው አካባቢዎች የደህንነት ጥበቃ ከማድረግ ጀምሮ የካሳ ጥያቄዎች እና የወሰን ማስከበር ጉዳዮችን ለመፍታት ክልሎችና በየደረጃው የሚገኙ አስተዳደራዊ መዋቅሮች ሚናቸው የጎላ መሆኑን ሥራ አስፈጻሚው ገልፀዋል፡፡

የዋና ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሙላት ገዛህኝ በበኩላቸው በክልሉ እየተከናወኑ ስለሚገኙ የኤሌክትሪክ ኃይል ግንባታ ፕሮጀክቶች እና በተቋሙ ላይ እያጋጠሙ ስላሉ ችግሮች በዝርዝር ለክልሉ የሥራ ኃላፊዎች አብራርተዋል፡፡

ኃላፊው እንደገለጹት በክልሉ በ10 ቢሊዮን ብር ሁለት የኃይል ማመንጫ ፕሮጄክቶች እና ከ16 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ በሚደርስ ወጪ ሰባት የማስተላለፊያ መስመርና ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክቶችን ግንባታ በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

ይሁን እንጂ በነባርና አዲስ በሚገነቡ የኤሌክትሪክ መሰረተልማቶች ላይ የሚፈጸሙ የስርቆት ወንጀሎች ተቋሙን ለከፍተኛ ኪሳራ እየዳረጉትና ፕሮጀክቶችንም እያጓተቱ ስለመሆኑን ገልጸዋል።

ከ2016 በጀት ዓመት በፊት በነበሩ ሁለት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ በስርቆት ብቻ 76 ነጥብ 07 ሚሊዮን ብር በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን የጠቀሱት አቶ ሙላት የደረሠው ጉዳት ኃይል ባለመሸጡ የደረሠውን ኪሳራ አያካትትም ብለዋል።

በተጨማሪም የወሰን ማስከበር ችግሮች እና ያልተገባ የካሳ ክፍያ መጠየቅ እንዲሁም በሠራተኞች ላይ የሚደርሱ የፀጥታ ስጋቶች በተቋሙ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ትልቅ እንቅፋት እየፈጠሩ መሆኑን አስረድተዋል።

ከክልሉ የተለያዩ ዘርፎች የተውጣጡ የሥራ ኃላፊዎች ተቋሙ ባነሳቸው ጉዳዮች ላይ ምላሽ ተሰጥተዋል።

በምላሻቸውም በክልሉ ልማትን የሚያውኩ አሠራሮችን እንደማይታገሱና ለኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ጥበቃ ከተቋሙ ጋር በቅንጅት እንደሚሠሩ ኃላፊዎች አረጋግጠዋል።

የኦሮሚያ ክልል መሬት አስተዳደር ምክትል ቢሮ ኃላፊና የህግና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ቢያ ራያ እንደገለፁት የሀገር ሀብት በሆኑ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚፈጸሙ ስርቆቶችን ለማስቀረት እና የሚታዩ የህግና አፈጻጸም ክፍተቶችን ለማረም ክልሉ ትኩረት ሰጥቶ ይሠራል።

በክልሉ የልማት ተነሽዎች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ አለማየሁ ተስፋ በበኩላቸው ካሳ የተከፈለባቸውን የተቋሙ ይዞታዎች ለማስከበር እና ተገቢ ያልሆነ ካሳ በመጠየቅ ፕሮጀክቶችን የሚያጓትቱ አካሄዶችንም ለማረም ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ተቋሙ በክልሉ የሚያከናውናቸው ፕሮጀክቶች ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነት ጥያቄዎች የሚመልሱ በመሆናቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ በምክክሩ ማጠቃለያ እንደ ገለፁት ተቋሙ የሚያከናውናቸው የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ግንባታዎች ኢኮኖሚያዊ፣ፓለቲካዊና ማህበራዊ ፋይዳቸው የላቀ በመሆኑ መንግስትና ህብረተሰቡ ጥበቃ ሊያደርጉላቸው ይገባል።

እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገለፃ ተቋሙ ከከልሉ መንግስት ጋር ተቀራርቦ በመስራት የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ለማሳደግ ወደ ፊትም ትኩረት ሠጥቶ ይሠራል።

Scroll to Top