ተቋሙ የማማከር ሥራ ይሁንታ ከዓለም ባንክ አገኘ

ተቋሙ የማማከር ሥራ ይሁንታ ከዓለም ባንክ አገኘ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በዓለም ባንክ ፋይናንስ በሚከናወኑ ፕሮጀክቶች ላይ የኢንጂነሪንግ የማማከር ሥራዎችን በራሱ አቅም እንዲያከናውን ከባንኩ ይሁንታ ማግኘቱን በተቋሙ የኢንጅነሪንግ ዘርፍ አስታወቀ፡፡

በዘርፉ የማስተላለፊያ መስመሮች ሲስተም ዲዛይን መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ፍቃዱ እንደገለፁት ከዓለም ባንክ ጋር በተደረጉ ተደጋጋሚ ውይይቶች ተቋሙ የማማከር ሥራውን በራሱ አቅም እንዲያከናውን ከስምምነት ተደርሷል ፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በሰርቬይንግ ፣ በቅድመ ዲዛይን፣ በቴክኒካል ስፔሲፊኬሽን ዝግጅት፣ በፍላጎት መግለጫ፣ በኮንትራት አስተዳደር እና የኮንስትራክሽን ቁጥጥር ሥራዎችን በራስ አቅም እንዲያከናወን ፈቃድ መገኘቱንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

የኢንጂነሪንግ ዘርፉ የአቅም ማሳደጊያ ፕሮግራምን በመቅረፅ የተለያዩ ስልጠናዎችን ለባለሙያዎች እንዲሰጥ በማድረግና ፣የቴክኒካል ስፔሲፊኬሽን ዝግጅት ላይ የነበሩ ክፍተቶችን በማስቀረት እና ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን በማድረግ ረገድ ለውጥ መታየቱን ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅት የሳይት የግንባታ ቁጥጥር ሥራና የኮንትራክት አስተዳደር ሥራዎችን በተሻለ ቅልጥፍናና ወጥነት ባለው መልኩ ማከናወን መጀመሩን አስረድተው የኢንጂነሪንግ ክፍሉ በአዲስ መልኩ መደራጀት ለዚህ ስኬት እንዳበቃውም ገልፀዋል፡፡

በዓለም ባንክ ፋይናንስ በሚሰሩ ፕሮጀክቶች እንደ ወራቤ ቡታጅራ የማስተላለፊያና ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ ፐሮጀክት፣ ፕሮቴክሽን ሪፍሬሽመንት ፕሮጀክት እና በራስ ፋይናንስ እየተሰሩ ባሉ ፕሮጀክቶች አፈፃፀማቸው ተገምግሞ በራስ የማማከር ዕድሉ እንደተገኘ አብራርተዋል፡፡

ተቋሙ ሙሉ የማማከር ሥራ ማግኘቱ የነደፈውን የሶስት ዓመት የስትራቴጂ ዕቅድ ለማሳካት እና የውጭ ምንዛሬን ለማዳን አስተዋጽዖ እንደሚኖረው አቶ ያሬድ አስረድተዋል፡፡

Scroll to Top