የኮይሻ የውኃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ያከናወናቸው የማህበራዊ ኃላፊነት ሥራዎች በግብርና ሥራቸው ምርታማ እንዲሆኑ እንዳስቻላቸው በጎፋ ዞን መሎ ኮዛ ወረዳ የባንካ ቀበሌ አርሶ አደሮች ገለጹ።
የአካባቢው ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ደነቀ ደስታ እንደገለጹት ፕሮጀክቱ ከመጀመሩ በፊት በአካባቢው የመንገድን መሰረተ-ልማት ችግር የነበረ በመሆኑ ነዋሪው እርስ በእርስ ለመገናኘትና አካባቢውን አልምቶ ወደ ገበያ ለማውጣት አስቸጋሪ ነበር።



በተለይም በኦሞ ወንዝ ላይ ድልድይ ባለመኖሩ የኮንታንና የጎፋ ሕዝቦችን ከመለየቱም በላይ ታላቅ ወንድማቸውን ጨምሮ በርካታ ሠዎች በውኃ ሙላት ተወስደው ሕይወታቸው ማለፉን አስታውሰዋል።
የኮይሻ ፕሮጀክት በኦሞ ወንዝ ላይ ሁለቱን ሕዝቦች የሚያገናኝ ድልድይ እና መንገድ በመስራት የአካባቢው ማህበረሰብ ከምርቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ማስቻሉን ጠቁመዋል።
በፕሮጀክቱ አማካኝነት የተገነባው የመንገድ መሠረተ-ልማት የአካባቢው ዋነኛ መገለጫ የሆነው የሙዝ ልማትና ሽያጭ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲያድግ በማድረግ የላቀ የገበያ ትስስርና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ይዞ መምጣቱን አቶ ደነቀ ጨምረው ገልጸዋል።
አርሶ አደር ማቴዎስ ጳውሎስ በበኩላቸው አካባቢው ሙዝን ጨምሮ ሰሊጥ፣ ዝንጅብል፣ ቡና እና አቮካዶ የመሳሰሉ ምርቶች በስፋት ቢገኙም መንገድ ባለመኖሩ ምክንያት አርሶ አደሩ በሚፈለገው መልኩ ተጠቃሚ ሳይሆን መቆየቱን አብራርተዋል።



አሁን ላይ ግን በፕሮጀክቱ አማካኝነት መንገድ በመሠራቱ በአካባቢው የሚመረቱ የግብርና ውጤቶች የአካባቢውን ገበያ አልፈው ከባኮ ቀበሌ ብቻ በቀን እስከ 30 በሚሆኑ ተሽከርካሪዎች ምርታቸውን እስከ ባህርዳር ድረስ መሸጥ መጀመራቸውን ተናግረዋል።
ይህ የገበያ ትስስር አርሶ አደሩን በቀጥታ ተጠቃሚ ከማድረጉም በላይ በርካታ የአካባቢው ወጣቶች በጭነትና በንግድ ሥራዎች ላይ ተሰማርተው የሥራ ዕድል እንዲያገኙ መንገድ ከፍቷል ብለዋል።
የባንካ ገራሃስቴ ቀበሌ ሊቀመንበር አቶ ደመላሽ አየለ ለረጅም ጊዜ በአካባቢው መንገድን ጨምሮ ሌሎች መሠረተ ልማቶች ያልነበሩ በመሆኑ ሕብረተሰቡ ለተደጋጋሚ ችግሮች ተጋልጦ ቆይቷል ብለዋል።
የኮይሻ ፕሮጀክት ወደ አካባቢው ሲመጣ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የገባውን ቃል በመፈጸም አሁን ላይ በአካባቢው በርካታ የመሠረተ ልማት ሥራዎችን ማከናወን መቻሉን አረጋግጠዋል።
ቀደም ሲል አርሶ አደሩ ምርቱን የሚወስድለት አካልና የገበያ አማራጭ ባለመኖሩ ምርቱን በስፋት የማምረት ፍላጎት እንዳልነበረው የጠቆሙት አቶ ደመላሽ ዛሬ ላይ ግን ተሽከርካሪዎች እስከ አርሶ አደሩ ማሳ ድረስ እየገቡ ምርቱን በቀጥታ በመጫን ላይ በመሆናቸው የአካባቢው አርሶ አደር በነፃነትና በስፋት ማምረት መጀመሩን አብራርተዋል።
ይህም ፕሮጀክቱ በአካባቢው የግብርና ምርታማነት ላይም አዲስ ምዕራፍ በመክፈቴ በማህበረሰቡ የገቢ እድገት ላይ ከፍተኛ መና መጫወቱን ነው የገለጹት።
የኮይሻ ፕሮጀክት ከመንገድ ግንባታ በተጨማሪ በአካባቢው ዘመናዊ ትምህርት ቤቶችንና አገልግሎት ሰጭ ተቋማትን በመገንባት ታሪካዊ ኃላፊነቱን መወጣቱንም አስገንዝበዋል።
በተለይም ተሽከርካሪዎች በቀላሉ ወደ ቀበሌው መግባት በመቻላቸው አስቸኳይ የሕክምና ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ወገኖች ሕይወት እየታደገ ይገኛል ብለዋል።
የባንካ ሕዝብ አሁን በግብርና ምርትና በተለያዩ መሠረተ-ልማቶች ተጠቃሚ መሆኑን የገለጹት ነዋሪዎቹ ለዚህም ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና ለዊ ቢውልድ ምስጋና አቅርበዋል።


