የፕሮጀክቱ የግንባታ ሥራ በፍጥነት እየተከናወነ ነው፤

የፕሮጀክቱ የግንባታ ሥራ በፍጥነት እየተከናወነ ነው፤

የኮይሻ የውኃ ኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ ሥራ በፍጥነትና በጥራት እየተከናወነ መሆኑን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የፕሮጀክቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ገለጹ፡፡

ምክትል ሥራ አስኪያጁ ኢንጂነር አባይነህ ጌትነት እንደገለጹት የኃይል ማመንጫ ግድቡ ከባህር ወለል በላይ 179 ሜትር ቁመት እና 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ የመያዝ አቅም እንዲኖረው ሆኖ በፍጥነት እየተገነባ ይገኛል።

ቀደም ባለው ጊዜ በፋይናንስ እጥረት ምክንያት የግንባታ መዘግየቶች አጋጥመውት የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ መንግስት ቀጥተኛ የፋይናንስ ድጋፍ በማድረጉ እና ተቋማዊ የክፍያ አፈጻጸሞች በመሻሻላቸው ያለ ምንም የፋይናንስ ችግር ግንባታው እየተፋጠነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በግድቡ የተለያዩ አካላት ላይ የሚከናወኑ የግንባታ ሥራዎች በመርኃ ግብራቸው መሰረት እየሄዱ ይገኛሉ ያሉት ኢንጂነር አባይነህ ከውጭ የሚመጡ አስፈላጊ ግብዓቶችም ያለምንም መቆራረጥ ወደ ሣይቱ እየገቡ ሥለመሆኑ አብራርተዋል።

ተቋሙ ከፕሮጀክቱ አማካሪ ድርጅቶች ጋር በመሆን በሁሉም የግንባታ ምዕራፎች ላይ የጥራት ቁጥጥር ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑንና በዚህ ሂደት ተቋሙ ወደፊት በራሱ አቅም ለሚያከናውናቸው ሜጋ ፕሮጀክቶች ትልቅ የውስጥ አቅም እየተፈጠረ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ሜጋ ፕሮጀክቶች ከፍተኛ የሀገር ሀብት የሚፈስባቸውና ዘመናዊ የምህንድስና ዕውቀቶች በተግባር የሚተረጎሙባቸው ማዕከላት መሆናቸውን ያስታወሱት ምክትል ሥራ አስኪያጁ ፕሮጀክቱ በዕውቀት ሽግግር በኩል ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ሥለመሆኑም ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የፕሮጀክቱ ሲቪል መሐንዲስ ይታገሱ አያሌው ትልቁን የግንባታ ድርሻ በሚይዘው በዋናው ግድብ ላይ የኮንክሪት ሙሊት (RCC) ሥራ ጥራቱን ጠብቆ 24 ስዓት እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

ከሲቪል ሥራው በተጓዳኝ በዋናው ግድብ የውኃ መግቢያ (Intake) እና ከግድቡ ወደ ኃይል ማመንጫ ቤቱ ውኃ ማስተላለፊያ ቱቦ (Penstock) ላይ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ገጠማና ብየዳ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኃይል ማመንጫ ቤቱ የመጀመሪያው ምዕራፍ የሲቪል ኮንክሪት ሙሊት ተጠናቆ በአሁኑ ወቅት የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎች መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡

የውኃ ማስተንፈሻ ቁፋሮውን በማጠናቀቅ የቁጥጥር መዋቅር (Control Structure) የኮንክሪት ሥራዎች በፍጥነት እየተከናወኑ እንደሚገኙ አረጋግጠዋል።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የፕሮጀክቱ ሜካኒካል መሐንዲስ ፉአድ ከድር በበኩላቸው የኃይል ማመንጫው እያንዳንዳቸው 300 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም ያላቸው ስድስት ተርባይኖች እንዳሉት ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት የሁለቱ ተርባይኖች የተከላ እንዲሁም ከግድቡ ወደ ሀይል ማመንጫ ቤት ውሀ የሚየስተላልፉ ቱቦዎች (Penstocks) ፍብረካና ተከላ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛል ብለዋል፡፡

2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዩሮ በጀት ተመድቦለት እየተከናወነ የሚገኘው የኮይሻ የውኃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ 1 ሺህ 800 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም የሚኖረው ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከ6 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሠራተኞች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡

Scroll to Top