ተቋሙ በቢሾፍቱ ከተማ የሚያስገነባውን የስልጠና ማዕከል ፕሮጀክት ለመጀመር የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ

ተቋሙ በቢሾፍቱ ከተማ የሚያስገነባውን የስልጠና ማዕከል ፕሮጀክት ለመጀመር የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በቢሾፍቱ ከተማ የሚያስገነባውን የስልጠና ማዕከል እና የአቅም ግንባታ ፕሮጀክት ሥራን ለመጀመር የሚያስችሉ የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን የፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አቶ እንዳለ የሺጥላ ገለጹ።

 አቶ እንዳለ እንደገለጹት ፕሮጀክቱ የተቋሙን የሰው ሀብት ሥራ አመራርና የስልጠና አቅርቦት በማዘመን እንዲሁም በዘመናዊ መሠረተ ልማቶችና ቴክኖሎጂዎች የተሟላ የማሰልጠኛ ማዕከል በመገንባት ተቋማዊ አቅምን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ያለመ ነው።

ፕሮጀክቱ በተቋሙ በብቃት ላይ የተመሠረተ የሰው ሀብት ሥራ አመራር ሥርዓት ለመዘርጋት፣ በሁሉም የሥራ ክፍሎች የሥርዓተ-ፆታ አካቶን ለማዳበር እንዲሁም የማዕከሉን አገልግሎት በኃይል ዘርፉ ለተሰማሩ የሀገር ውስጥና የውጭ አካላት ክፍት በማድረግ በኢትዮጵያና በቀጣናው ተመራጭ ለመሆን ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወትም ሥራ አስኪያጅ ገልጸዋል።

የስልጠና ማዕከሉ ቢሾፍቱ በሚገኘው የባለ 400 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ግቢ ውስጥ እንደሚገነባ ጠቁመው ለስልጠናና መማሪያ፣ ለአስተዳደር፣ ለወርክሾፕ እና ለተማሪዎች ማደሪያ እንዲሁም ለሌሎች መሰል አገልግሎቶች የሚውሉ 26 ዘመናዊ ህንፃዎችን በውስጡ እንደሚያካትትም አስረድተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም የግንባታ ሥራውን ለመጀመር የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።  ግንባታው የሚከናወንበትን ቦታ ነፃ ለማድረግ ከመሬት በላይ ያሉትን የኤሌክትሪክ መስመሮችን ወደ መሬት ውስጥ የመቀየር ሥራ በተቋሙ የኢንጅነሪንግና ኮንስትራክሽን ዘርፍ እየተከናወነ ነው፡፡

የማዕከሉን የዲዛይንና የግንባታ ሥራዎች የሚቆጣጠር አማካሪ ድርጅት ለመቅጠር የተከናወነው የቴክኒክ ግምገማ ተጠናቆ አሁን ላይ ከፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲ (AFD) የይሁንታ ምላሽ እየተጠበቀ እንደሚገኝ አቶ እንዳለ ተናግረዋል፡፡

ሥራ አስኪያጁ እንደገለጹት ከስልጠና ማዕከሉ የግንባታ ሥራ ጎን ለጎን በሰው ሀብት ሥራ አመራር ዘርፍ አዲስ የአሠራር ሥርዓት ለመዘርጋት እንዲሁም ለማዕከሉ የማስተማሪያ ማዕቀፎችን ለማዘጋጀት ‘ስፌሬ’ የተሰኘ የፈረንሳይ ቴክኒካል ድጋፍ ሰጪ አማካሪ ድርጅት ተቀጥሮ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛል።

በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ለሚተገበረው የስልጠና ማዕከል እና የአቅም ግንባታ ፕሮጀክት በአጠቃላይ 25 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዩሮ በጀት የተመደበ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 17 ሚሊዮን ዩሮው በፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲ (በብድርና እርዳታ)፣ 4 ሚሊዮን ዩሮው በአውሮፓ ሕብረት (በብድር) እንዲሁም 2 ሚሊዮን ዩሮ በተቋሙ የሚሸፈን ይሆናል። ቀሪውን የ2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዩሮ የበጀት ክፍተት ለመሙላት ከፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲ ባለድርሻ አካለት ጋር ንግግር እየተደረገ ስለመሆኑም ተናግረዋል።

 የስልጠና ማዕከል ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር በዓመት በአማካይ ለአንድ ሺህ ነባር እና 750 አዳዲስ ተቀጣሪዎችን በቅድመ-ሥራ ስልጠና የማስተናገድ አቅም ይኖረዋል ተብሏል፡፡

Scroll to Top