‹‹ድንበር ተሻጋሪ የኃይል ንግድን ለማሳለጥ የሚያስችሉ መሠረተ ልማቶች ተጠናቀዋል›› ኢንጂነር አሸብር ባልቻ

‹‹ድንበር ተሻጋሪ የኃይል ንግድን ለማሳለጥ የሚያስችሉ መሠረተ ልማቶች ተጠናቀዋል›› ኢንጂነር አሸብር ባልቻ

ድንበር ተሻጋሪ የኤሌክትሪክ ኃይል ንግድን ለማሳለጥና ቀጣናዊ ትስስሩን ለማጠናከር የሚያስችሉ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች መጠናቀቃቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ እና የምሥራቅ አፍሪካ የኃይል ትስስር የሥራ አስፈፃሚዎች ኮሚቴ ሰብሳቢ አስታወቁ፡፡

37ኛው የምስራቅ አፍሪካ የኃይል ትስስር የአመራር ኮሚቴ ልዩ ስብሰባ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡



ስብሰባው በአባል ሀገራቱ በቀረቡት የመንግሥታት እና የተቋማት የጋራ መግባቢያ ስምምነቶች እንዲሁም ተያያዥ የአስተዳደር ሰነዶች ማሻሻያ ሐሳቦች ላይ ለመምከር ያለመ ነው፡፡

በስብሰባው ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ እና የወቅቱ የምሥራቅ አፍሪካ የኃይል ትስስር የሥራ አስፈፃሚዎች ኮሚቴ ሰብሳቢ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ በአባል ሀገራቱ መካከል የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረትን በመቅረፍ አስተማማኝና ቀጣይነት ያለው የኃይል አቅርቦት እንዲኖር ለማስቻል ይሰራል ብለዋል፡፡

የኃይል መሠረተ ልማቶችን በጋራ በማልማት ቀጣናዊ ትስስር እንዲፈጠር እና ሀገራቱ የኤሌክትሪክ ኃይል ምርትን በነፃነት የሚገበያዩበት ድንበር ተሻጋሪ የኃይል ሽያጭ ሥርዓት እንዲዘረጋ በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባም ነው የተናገሩት፡፡

እንደ ኢንጂነር አሸብር ገለፃ የኤሌክትሪክ ኃይል ትስስሩን ይበልጥ ለማጠናከር የገቢያ ደንቦች፣ የአሰራር ሥርዓቶች እና የንግድ መድረኮች ዝግጁ ተደርገዋል፡፡

በቀጣናው ያለውን ሰፊ የውኃ፣ የንፋስ፣ የእንፋሎት እና የፀሐይ ኃይል አቅም አልምቶ ለመጠቀም በቅንጅት መሥራት አስፈላጊ መሆኑን አክለው ገልፀዋል፡፡

ውስብስብ የሆኑ ቀጣናዊ የኃይል ትስስር ጥያቄዎችን በተዘረጉ የአሠራር ሥርዓቶች መሠረት መመርመር የተቋማዊ ብስለት ምልክት እንደሆነም አንሰተዋል፡፡

በስብሰባው የቀረቡት ማሻሻያዎች የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በራሱ ሥልጣን የማይወስናቸው በመሆናቸው አንኳር ጉዳዮቹ ተለይተው ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እንደሚቀርቡ አስገንዝበዋል፡፡

Scroll to Top