ተቋሙ የቴክኒሺያኖች አቅም ለማጎልበት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል፤

ተቋሙ የቴክኒሺያኖች አቅም ለማጎልበት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል፤

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሲቪል እና ኤሌክትሮ ሜካኒካል ቴክኒሽያኖችን አቅም ቀጣይነት ባለው መልኩ ለመገንባት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ገለጸ፡፡

ተቋሙ ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከየካ ክፍለ ከተማ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ጋር በመተባበር በኢንጂነሪንግና ኮንስትራክሽን ቢዝነስ ዘርፍ በኮንስትራክሽን ማኔጅመንት መምሪያ ውስጥ የሚገኙ የሲቪል እና ኤሌክትሮሜካኒካል ኤሬክሽን ቴክኒሺያኖች አሰልጥኖ አስመርቋል።

የተቋሙን ዋና ሥራ አስፈፃሚ በመወከል በምረቃ ሥነ- ሥርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የሰው ኃይል ሥራ አስፈፃሚ አቶ አታላይ አበበ እንደተናገሩት ቴክኒሺያኖች በተግባር የተፈተነ ብቃት እንዲኖራቸው ለማድረግና አቅማቸውን ለማሳደግ ተቋሙ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል፡፡

ከሀገር ውስጥ ባለፈ በውጭ ሀገራት ጭምር የተሻለ የግንባታና የኦፕሬሽን ሥራዎችን ማከናወን የሚችልበት ደረጃ ላይ እንዲደረስ ተቋሙ አቅዶ እየሰራ መሆኑንና መሰል ሥልጠናዎችም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል፡፡

በኢንጂነሪንግና ኮንስትራክሽን ቢዝነስ ዘርፍ የሀብት አስተዳደር መምሪያ ዳይሬክተር ወ/ሮ መንበረ ክፍሌ በበኩላቸው ሥልጠናው በሥራ ያዳበሩትን የተግባር ክህሎት በንድፈ-ሐሳብና በትምህርት በማዳበር የሥራ አፈጻጸማቸውን ከፍ ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ ነው ብለዋል፡፡

ሠራተኞችን አቅም ቀጣይነት ባለው መልኩ ለመገንባት በኢንጂነሪንግ ዲዛይን፣ በሱፐርቪዥን ኮንትራት እና በግንባታ አስተዳደር ውስጥ የሚገኙ ሠራተኞችን ፍላጎት መሠረት በማድረግ የሥልጠና ዕቅድ ተዘጋጅቶ ለፓወር አካዳሚ መላኩን ተናግረዋል፡፡

በየካ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ የትምህርትና ስልጠና ምክትል ዲን የሆኑት አቶ ዛዲግ ከማል ኮሌጁ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር በመተባበር ለ53 ባለሙያዎች የ15 ቀናት ቲዎሪና ተግባር ተኮር ሥስልጠና መስጠታቸውን አብራርተዋል፡፡

ኮሌጁ በቀጣይም ከተቋሙ ጋር በመሰል የአቅም ግንባታ ሥራዎች ዙሪያ ተባብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

ሥልጠናውን ወስደው ላጠናቀቁ ባለሙያዎች የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።

Scroll to Top