‎በሪጅኑ የኃይል አቅርቦት አስተማማኝነትን ለማስቀጠል የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፤

‎በሪጅኑ የኃይል አቅርቦት አስተማማኝነትን ለማስቀጠል የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፤

‎‎በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ደቡብ ሁለት ሪጅን ያለውን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት አስተማማኝነት ለማስቀጠል የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን የሪጅኑ ዳይሬክተር ገለፁ።

‎ዳይሬክተሩ አቶ ምትኩ ታዬ እንደገለፁት ሪጅኑ በስምንት ማከፋፈያ ጣቢያዎችና 1 ሺህ 178 ኪሎ ሜትር በሚሸፍኑ የማስተላለፊያ መስመሮች ለኢትዮ-ኬኒያ ኮንቨርተር ጣቢያ ጨምሮ ለደቡባዊ የኢትዮጵያ ክፍል አስተማማኝ ኃይል እያቀረበ ይገኛል።

‎የአካባቢው የኃይል ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ከግምት በማስገባት በኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ የማዘመንና የአቅም ማሳደግ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

‎ቀደም ሲል ተጀምረው ሳይጠነቀቁ የቆዩት የሳውላ፣ ቀይ አፈር እና የወላይታ ሶዶ አንድ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች የመቆጣጠሪያ ብሬከር ወደ ጂአይኤስ (GIS) የመቀየር እንዲሁም የሀላባ ማከፋፈያ ጣቢያ የአቅም ማሳደግ ሥራዎች በ2018 በጀት ዓመት መጠናቀቃቸውን አቶ ምትኩ አብራርተዋል።

ከአቅም ማሳደግ እና ማዘመን ሥራዎች በተጨማሪ በሪጅኑ የአዳዲስ የኃይል መሠረተ ልማት ግንባታ ሥራዎች እየተከናወኑ ስለመሆኑም ጠቁመዋል።

የብሔራዊ ኤሌክትሪክ ደቡባዊ ግሪድ ማስፋፊያ ፕሮጀክት አካል የሆኑት የአርባ ምንጭ ሁለት ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ እና የወላይታ ሶዶ ሁለት ማከፋፈያ ጣቢያ የማስፋፊያ ሥራዎች ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን የገለፁት ዳይሬክተሩ ይህም የሪጅኑን የኃይል አቅርቦት አስተማማኝነት በማሳደግ በኩል ሚናቸው የጎላ መሆኑን አብራርተዋል።

‎የሽግዳን እና ቲርጋ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ግንባታ ተጠናቆ ወደ ሥራ ሲገቡ በአካባቢው ለሚገኙት ማህበረሰቦችና የስኳር ፋብሪካዎች በቂና አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት እንዲኖር ያስችላሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም አስረድተዋል።

‎የኢትዮ-ኬኒያ ኮንቨርተር ጣቢያ ማስተላለፊያ መስመርን ጨምሮ በሪጅኑ የሚገኙ መሰረተ ልማቶችም ላይ የዕቅድና ድንገተኛ የፍተሻ እንዲሁም የጥገና ሥራዎች በተጠናከረ ሁኔታ እየተከናወኑ መሆኑንም ገልፀዋል።

‎በበጀት ዓመቱ ምቹ የሥራ ከባቢን ከመፍጠር አንፃር በወላይታ ሶዶ ሁለት፣ በሳውላ፣ በቀይ አፈር እና በአርባ ምንጭ ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ የሠራተኛ መኖሪያ ቤቶች፣ የመቆጣጠሪያ ክፍሎች እና የአጥር እድሳት ሥራዎች መከናወናቸውንም ጨምረው ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

Scroll to Top