ተቋሙ ለተለያዩ ተቋማት የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን እየሰጠ ይገኛል

ተቋሙ ለተለያዩ ተቋማት የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን እየሰጠ ይገኛል

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በተለያዩ ዘርፎች ለመንግሥታዊና መንግሥታዊ ላልሆኑ ተቋማት የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን መስጠት መጀመሩን በተቋሙ የኢትዮ ፓወር አካዳሚ አስታወቀ፡፡

ተቋሙ ላለፉት አምስት ቀናት “በኤሌክትሪካል ፓወር ሲስተም ኦፕሬሽን፣ ጥገናና ፕሮቴክሽን” ጉዳዮች ላይ ለንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የኤሌክትሪክ ሲስተም ኦፕሬሽንና ጥገና ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና ሰጥቷል፡፡

የኢትዮ ፓወር አካዳሚ ዳይሬክተር ወንድወሰን ካሳ (ዶ/ር) በስልጠናው ማጠናቀቂያ ወቅት እንደተናገሩት የተቋሙ አካዳሚ በአቅም ግንባታ ሥራዎች የረጅም ጊዜ ልምድ አለው።

በዚህም በኃይል ዘርፉ በርካታ ባለሙያዎችን ከማፍራቱም ባሸገር ለሌሎች ተቋማት የተለያዩ ስልጠናዎችን ለመስጠት መብቃቱን ገልፀዋል ።

አካዳሚው  እስካሁን ንብ ኢንተርናሽናል ባንክን ጨምሮ ለኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና መስጠቱን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ስልጠናው በሁለቱ ተቋማት መካከል ልምድ ለመለዋወጥ እንደሚያግዝ ጠቅሰው ተቋሙ በዘርፉ ያለውን ልምድና አቅም እንዲያካፍል በባንኩ በመመረጡም አመስግነዋል፡፡

በቀጣይ ከባንኩ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች በትብብር የመስራቱ ሁኔታ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡

ለተቋማቱ እየተሰጠ ያለው የአቅም ግንባታ ስልጠና ተቋሙ በዘርፉ ያለውን አቅም ለሌሎች በማካፈል ለሀገር ግንባታ አስተዋጽኦ ለማድረግ እና ተቋሙን ለማስተዋወቅ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው  ዶ/ር ወንድወሰን አብራርተዋል፡፡

አካዳሚው በቀጣይ በኤሌክትሪክ ኃይል ዘርፍ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የተለያዩ ዘርፎች ለተቋማት ስልጠናዎችን ለመስጠት አቅዶ እየሰራ እንደሆነም ዱይሬክተሩ ገልፀዋል ።

በንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የህንፃ አስተዳደርና ኪራይ ዳይሬክተር አቶ ሀብተማሪያም ተስፋዬ በበኩላቸው ተቋሙ በዘርፉ ያለውን ልምድ ለባንኩ ማካፈሉን አመስግነው ስልጠናው የባለሙያዎችን ክህሎትና እውቀት በማሳደግ የባንኩን አሰራር ወደፊት ያራምዳል ብለዋል።

ስልጠናው በባንኩ ህንፃ የኤሌክትሪክ ሲስተም ላይ ለሚያጋጥሙ ችግሮች በቀላሉ መፍትሔ በመስጠት እና አሰራሮችን በማቀላጠፋ ባንኩ የያዘውን ስትራቴጅክ ግብና ፍኖተ ካርታ ለማሳካት በግብዓትነት እንደሚያግዝም ጠቅሰዋል።

ስልጠናውን ከወሰዱት መካከል በባንኩ ሲኒየር የህንፃ ቴክኒሽያን የሆኑት አቶ ተስፋቸው ደምስ ከስልጠናው ሥራቸውን በምን መልኩ ማከናወን እንዳለባቸው እንዲሁም ችግሮች ሲያጋጥሙ እንዴትና በምን መልኩ መፍታት እንደሚቻል የሚያግዝ  ግንዛቤ መቅሰማቸውን ተናግረዋል፡፡

ስልጠናው በንድፈ ሃሳብና በተግባር በተደገፈ መልኩ መሰጠቱ ተገልጿል።

Scroll to Top