የ‎ኮንቨርተር ጣቢያው የተቋሙን ርዕይ ማሳካት በሚያስችል ቁመና ላይ ይገኛል፤‎

የ‎ኮንቨርተር ጣቢያው የተቋሙን ርዕይ ማሳካት በሚያስችል ቁመና ላይ ይገኛል፤‎


የኢትዮ ኬኒያ ባለ 500 ኪሎ ቮልት ኮንቨርተር ማከፋፈያ ጣቢያ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የአፍሪካ የታዳሽ ኃይል ማዕከል ለመሆን የያዘውን ርዕይ ለማሳካት በሚያስችል አስተማማኝ ቁመና ላይ እንደሚገኝ የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ ገለፁ።‌‎

ሥራ አስኪያጁ አቶ ሀብታሙ ግርማ እንደገለፁት ከወላይታ ሶዶ ከተማ በ7 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ጣቢያው እስከ ኬኒያ የተዘረጋውን 1 ሺ 45 ኪሎ ሜትር የማስተላለፊያ መስመር በመጠቀም 2 ሺህ ሜጋ ዋት ኃይል ለጎረቤት ሀገራት የማስተላለፍ አቅም ይዞ 2014 ዓ.ም ላይ ወደ ኦፕሬሽን ገብቷል።‌‎

ጣቢያው የተገነባበት የቴክኖሎጅ ዓይነት የኤሌክትሪክ ፍሰቱ ሳይወዛወዝ ወደ አንድ አቅጣጫ ብቻ ቀጥ ብሎ የሚጓዝበት ቀጥተኛ የኤሌክትሪክ ዥረት (Direct Current – DC) መሆኑ ተጨማሪ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎችንና የማከፋፈያ ጣቢያዎችን ግንባታ በማስቀረት ከፍተኛ ወጪ እንዲድን ማስቻሉን ጠቁመዋል።‎

‎ጣቢያው በኤሌክትሪክ ፍሰት መለዋወጥ (Frequency) ልዩነት ምክንያት አጠቃላይ የሀገሪቱ የኃይል ቋት (Power Grid) እንዳይረበሽ የሚከላከል ከመሆኑም በላይ በማስተላለፊያ መስመሩ ላይ የሚኖረውን የኤሌክትሪክ ብክነት በከፍተኛ ሁኔታ የሚቀንስ መሆኑን ሥራ አስኪያጁ ገልፀዋል።
‌‎
በአሁኑ ወቅት ለኬኒያና ለታንዛኒያ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ በተደረገው ስምምነት መሰረት 300 ሜጋ ዋት ኃይል በአስተማማኝ ሁኔታ እያስተላለፈ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡‌‎

በስምምነቱ መሠረት የሚቀርበው የኃይል መጠን በየጊዜው እያደገ የሚሄድ በመሆኑ አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ቅድሚያ ተሰጥተው እየተከናወኑ ስለመሆኑ ጠቁመዋል።

የኤሌክትሪክ መስመሩ ያለምንም መቆራረጥ ኃይል ማስተላለፉን እንዲቀጥል መስመሩ ከሚያልፍባቸው ክልሎች ጋር በመቀናጀት ተከታታይ የጥገናና የኢንስፔክሽን ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን የገለፁት አቶ ሀብታሙ በተጨማሪም በውሉ መሰረት ከኬኒያ ባለሙያዎች ጋር በመተባበር የፍተሻና የጥገና ሥራዎች ይከናወናሉ።

ተቋሙ ከኬኒያና ታንዛኒያ ባሻገር ለሌሎች አጎራባች ሀገራት ኃይል በማቅረብ የአፍሪካ የታዳሽ ኃይል ማዕከል ለመሆን የሚያደርገውን ጥረት ለማሳካት ጣቢያው ያለው ሚና እንዳለው አስገንዝበዋል።‌‎

ይህንን ሚናውን በብቃት ለመወጣትና ክፍለ-አህጉራዊ የኃይል ትስስርን በማጠናከር ለሌሎች የኃይል መሠረተ ልማቶች ግንባታ የሚውል የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ አቅዶ እየሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡‌‎

የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ሥልጠና በማመቻቸት የጣቢያውን ባለሙያዎች አቅም ቀጣይነት ባለው መልኩ ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን ያስታወሱት አቶ ሀብታሙ የዕውቀት ሽግግር እንዲኖር በማድረግ የኦፕሬሽንና የጥገና ሥራዎች በራስ አቅም እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።‎

ይህ ባለ 500 ኪሎ ቮልት ‎የኮንቨርተር ማከፋፈያ ጣቢያ ከዓለም ባንክ፤ ከአፍሪካ ልማት ባንክ በተገኝ ብድር እና ከኢትዮጵያ መንግስት በወጣ ወጪ በ214 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በጀት የተገነባ መሆኑ ይታወሳል።

Scroll to Top