በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የወላይታ ሶዶ ሁለት ባለ 400 ኪሎ ቮልት ማከፋፈያ ጣቢያ ለአካባቢውና ለደቡባዊ ግሪድ ዋነኛ የኃይል ማዕከል በመሆን እያገለገለ እንደሚገኝ የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ ገለጹ።
ሥራ አስኪያጁ አቶ በላይነህ ህንዳሞ እንደገለጹት ጣቢያው ከጊቤ ሦስት የሚመነጨውን 1 ሺህ 870 ሜጋ ዋት ኃይል የሚቀበል ሲሆን ከግልገል ጊቤ ሁለት እንዲሁም በይርጋለም ቁጥር ሁለት በኩል ደግሞ ከገናሌ ዳዋ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ጋር በቀጥታ የተገናኘ ነው።
ከኃይል ማመንጫዎች ከሚቀበለው ኃይል ውስጥ 60 ከመቶ የሚሆነውን በቀጥታ ለገላን ማከፋፈያ ጣቢያ እንደሚሰጥ ገልጸዋል።
በባለ 132 ኪሎ ቮልት ለሀላባ እና ለወላይታ ቁጥር አንድ፣ በባለ 230 ኪሎ ቮልት ለአዲሱ የአርባ ምንጭ ቁጥር ሁለት ማከፋፈያ ጣቢያዎች እንዲሁም በ33/15 ኪሎ ቮልቶች ለዳታ ማይኒንግ ድርጅቶችና ለኢትዮጵያ ኤእሌክትሪክ አገልግሎት የአካባቢው ዲስትሪክት እንደሚያቀርብም ጠቁመዋል።



አንደ አቶ በላይነህ ገለጻ በተጨማሪም ጣቢያው በአራት ባለ 400 ኪሎ ቮልት መስመር ለኢትዮ-ኬንያ ኮንቨርተር ማከፋፈያ ጣቢያ ኃይል ይሰጣል።
የኃይል አቅርቦቱን አስተማማኝነት ለማረጋገጥ የቅድመ ፍተሻ፣ የድንገተኛና በዕቅድ ላይ የተመሰረቱ የክትትልና የጥገና ሥራዎች ከሪጅኑ ጋር በመተባበር እየተከናወኑ በመሆኑ በአቅርቦት በኩል ምንም ዓይነት ስጋት እንደሌለ አብራርተዋል።
የብሔራዊ ኤሌክትሪክ ደቡባዊ ግሪድ ማስፋፊያ ፕሮጀክት አካል የሆነው የወላይታ ሶዶ ሁለተኛ ማከፋፈያ ጣቢያ የማስፋፊያ ሥራ ተጠናቆ ወደ ኦፕሬሽን መግባቱንም ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት ጣቢያው እያንዳንዳቸው 250 ሜጋ ቮልት አምፒዬር አቅም ያላቸው ሦስት አውቶ ትራንስፎርመሮች ያሉት ሲሆን አጠቃላይ አቅሙም 750 ሜጋ ቮልት አምፒዬር መድረሱ ተናግረዋል።



ከእነዚህ ትራንስፎርመሮች መካከል ሁለቱ የደቡባዊ ግሪድ ማስፋፊያ አካል ለሆኑት ለአርባምንጭ ቁጥር ሁለት እና ለሽግዳን ማከፋፈያ ጣቢያዎች ተብለው በቅርቡ የተገጠሙ መሆናቸውን አንስተዋል።
ጣቢያ አሁን ላይ ተጨማሪ የኃይል ጥያቄዎችን በብቃት ማስተናገድ የሚችል አቅም ያለው ቢሆንም በቀጣይ ሊኖሩ የሚችሉ የኃይል ፍላጎቶችን ታሳቢ በማድረግ አቅሙን ይበልጥ ለማሳደግ ታቅዶ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በዚህም መሠረት በ2019 በጀት ዓመት ተጨማሪ ባለ 250 ሜጋ ቮልት አምፒዬር አውቶ ትራንስፎርመር ለመትከል የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መጠናቀቃቸውን ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል።
የወላይታ ሶዶ ሁለት ማከፋፈያ ጣቢያ ለደቡባዊ ግሪድና ለኢትዮ ኬኒያ ኮንቨርተር ዋነኛ የኃይል ማዕከል በመሆኑ ከመለዋወጫ እቃ እጥረት ጋር ተያይዞ ያለው ችግር እልባት ሊሰጠው እንደሚገባ አቶ በላይነህ አሳስበዋል።


