የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የስትራቴጂክ ዕቅድና አፈፃፀምን ለመከታተልና ለማስተዳደር የሚያስችል “ኢ.ኢ.ፒ ቢ.ኤስ.ሲ” የተሰኘ የድረ-ገፅ መተግበሪያ በሥራ ላይ ለማዋል እየሰራ መሆኑን የዲጅታል ትራንስፎርሜሽን ዘርፍ አስታወቀ፡፡
የዘርፉ ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ጽዮን በቀለ እንደተናገሩት መተግበሪያው የተቋሙን የዕቅድ አፈጻጸም ምዘናዎች በቴክኖሎጂ እንዲታገዙ በማድረግ የቆየውን ወረቀት ተኮር አሠራር ሙሉ በሙሉ የሚያስቀር ነው።

የዲጅታል ትራንስፎርሜሽን ዘርፍ ሥራ አስፈጻሚ
መተግበሪያው የተቋሙን ስትራቴጂካዊ ግቦች፣ የሥራ ክፍሎችንና የሠራተኞችን የሥራ አፈፃፀም ደረጃ በዲጂታል ሥርዓት ለመከታተልና ለመገምገም ከፍተኛ እገዛ ያደርጋልም ብለዋል።
የአሠራር ሥርዓቱ ከዚህ በፊት የነበሩትን የወረቀትና የተበታተኑ የሪፖርት ማቅረቢያ መንገዶችን በማስቀረት ሥራዎችን በጥራት፣ በፍጥነትና ያለሰው ንክኪ ለመከታተል እንደሚያስችልም ነው ያብራሩት፡፡
እንደ ሥራ አስፈፃሚዋ ገለፃ በተቋሙ ውስጥ ግልፅነትን፣ ተጠያቂነትን እና በመረጃ ላይ የተመሰረተ የውሳኔ አሰጣጥን ለማስፈን መተግበሪያው የስትራቴጂክ ዕቅድ አስተዳደር እና የቁልፍ አፈፃፀም አመልካቾች (KPI) ሥርዓቶችን ያካተተ ነው።
መተግበሪያው ከተቋሙ ዋና የሰው ኃይልና የፋይናንስ መረጃ ቋት (SAP Integration) እንዲሁም ከማዕከላዊ የተጠቃሚዎች ማውጫ (Active Directory) ጋር ሙሉ በሙሉ የተቀናጀ የቁጥጥር ሥርዓት ያለው መሆኑን የጠቀሱት ወ/ሮ ጽዮን የአሠራር ሥርዓቱ ወደ ትግበራ ከመግባቱ በፊትም የሠራተኞችንና የተቋሙን መረጃ ደኅንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠበቅ ታስቦ ጥብቅ የሳይበር ደኅንነት (Cyber Security) ፍተሻዎችን ማለፉንም ተናግረዋል፡፡

እንደ ሥራ አስፈፃሚዋ ገለፃ አዲሱ አሠራር በሥራ ላይ በሚውልበት ወቅት ዕቅዶችና የውሳኔ ማጽደቅ ሂደቶች ሙሉ በሙሉ በኢንተርኔት የሚከናወኑ በመሆኑ ምንም ዓይነት የህትመትና የወረቀት ወጪዎችን በማስቀረት የታተሙ ሰነዶች እንዳይኖሩ ያደርጋል።
በተጨማሪም እያንዳንዱ ሠራተኛ በየዕለቱ የሚከናውናቸውን የሥራ እንቅስቃሴዎች በሲስተሙ ላይ ስለሚመዘግብ ለሚመለከታቸው የሥራ ክፍሎችና ለቦርድ አባላት ትክክለኛና ወቅቱን የጠበቀ ሪፖርት በጊዜው እንዲደርስ እንደሚያስችልም ጠቁመዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የመተግበሪያው 80 በመቶ ሥራዎች መጠናቀቃቸውን የገለጹት ሥራ አስፈጻሚዋ ቀሪው 20 በመቶ ደግሞ ከተጠቃሚዎችና ከሚመለከታቸው አካላት የሚሰበሰቡ ግብረ-መልሶችን በማካተት ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ለማስገባት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በቀጣይም በአሠራር ሥርዓቱ ላይ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን (AI) በማካተት መተግበሪያው ራሱ ግምገማ እንዲሠራ የማድረግ ዕቅድ እንዳለም ወ/ሮ ጽዮን ተናግረዋል።
