የኃይል መሠረተ ልማቶች እንዲጠበቁ የአካባቢው ማህበረሰብ ሚናውን መወጣት አለበት፤

የኃይል መሠረተ ልማቶች እንዲጠበቁ የአካባቢው ማህበረሰብ ሚናውን መወጣት አለበት፤

በአካባቢው የሚገኙ የኤሌክትሪክ ኃይል መሠረተ ልማቶችን በመጠበቅ በኩል ማህበረሰቡ ሚናውን ሊወጣ እንደሚገባ የወላይታ ሶዶ ከተማ ከንቲባ ገለፁ።

ከንቲባዋ ወይዘሮ እታገኝ ኃይለማሪያም እንደገለፁት በወላይታ ሶዶ ከተማና ዙሪያዋ የኢትዮ ኬኒያ ኮንቨርተር ጣቢያን ጨምሮ ሌሎች ሁለት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎችና የማስተላለፊያ መስመሮች ይገኛሉ።

ሁለቱ ማከፋፈያ ጣቢያዎች የከተማዋንና የአካባቢውን የኃይል ፍላጎት በአስተማማኝ መልኩ በማሟላት በኩል ሚናቸው የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኃይል አቅርቦቱ አካባቢው ባለው የመልማት አቅም ልክ እንዲለማና የኢንቨስትመንት ፍሰቱ እንዲጨምር በማስቻል የንግድና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች በፍጥነት እንዲያድጉ ማድረጉን አብራርተዋል።

በአካባቢው ያለው የኃይል አቅርቦት ከተማዋን ለማዘመንና ስማርት ከተማ ለማድረግ እንዲሁም የሕብረተሰቡን የአኗኗር ዘይቤ ለመለወጥ ለሚከናወኑ ሥራዎች ምቹ መደላድል መፍጠሩንም ተናግረዋል።

አሁን ላይም በከተማዋ ያለውን የኃይል አቅርቦት ከግምት በማስገባት ከፍተኛ ኃይል የሚፈልጉና ሰፊ የሥራ እድል የሚፈጥሩ የኢንቨስትመንት ጥያቄዎች ለከተማ አስተዳደሩ እየቀረቡ መሆኑን አስታውሰዋል።

እነዚህ የኃይል መሠረተ ልማቶች ከፍተኛ ሀገራዊ ሀብት የወጣባቸው መሆኑን ያወሱት ከንቲባዋ መሠረተ ልማቶቹ ለአካባቢውና ለሀገር የሚሰጡትን ጥቅም ከግምት በማስገባት ከስርቆት መከላከል ላይ ማህበረሰቡ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የከተማ አስተዳደሩም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ግንዛቤ ከመፍጠር ባለፈ ሥርቆት በሚፈፅሙ አጥፊዎች ላይ የሚያደርገውን ክትትልና ቁጥጥር አጠናክሮ እንደሚቀጥል ወ/ሮ እታገኝ አረጋግጠዋል።

የወላይታ ሶዶ ኮንቨርተር ጣቢያው ለኬኒያና ታንዛኒያ ኃይል በማቅረብ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ተመስርቶ ለማደግ እና ኢትዮጵያ የአፍሪካ የታዳሽ ኃይል ማዕከል ለመሆን የያዘችውን ዕቅድ የሚያሳልጥ ግዙፍ የኃይል መሰረተ ልማት ነው።

Scroll to Top