በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በአርባ ምንጭ ዙሪያ ተገንብተው በመጠናቀቅ ላይ የሚገኙ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር እና ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክቶች በአካባቢው አስተማማኝ ኃይል ለማቅረብ እንደሚያስችሉ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የአርባ ምንጭ ሪጅን ገለፀ።
የሪጅኑ ዳይሬክተር አቶ ገረመው ወንድምሁነኝ እንደገለፁት አሁን ላይ የአርባ ምንጭ ከተማን ጨምሮ የጋሞ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች በከተማው ውስጥ ከሚገኘው የነባሩ የባለ 132 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ኃይል በማግኘት ላይ ይገኛሉ።

የማከፋፈያ ጣቢያው በዞኑ ለሚገኙ ኢንዱስትሪዎች፣ ለአገልግሎት ሰጭና መንግስታዊ ተቋማት እንዲሁም ለነዋሪው ኃይል የማቅረብ አቅም ቢኖረውም በአንድ አቅጣጫ ብቻ ኃይል የሚያገኝ በመሆኑ መስመሩ በተለያዩ ምክንያቶች ችግር ሲያጋጥመው የኃይል መቋረጥ ይስተዋልበት እንደነበር አስታውሰዋል።
በተጨማሪም በአካባቢው ካለው የኃይል ፍላጎት ዕድገት ጋር ተያይዞ በቀጣይ ሊመጡ የሚችሉ የኃይል ጥያቄዎችን በአግባቡ ማስተናገድ እንደማይችል ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።
ይሁንና በጣቢያው ላይ እየተከናወነ ባለው የማስፋፊያ ሥራ በሌላ አቅጣጫ ኃይል እንዲያገኝ በማደረግ በቀለበት ሥርዓት መያያዙ፤ ከመስመሩ ጋር ተያይዞ ይስተዋሉ የነበሩ የኃይል መቆራረጦችን ሙሉ በሙሉ በመቅረፍ አስተማማኝ ኃይል ለማቅረብ ያስችላል ነው ያሉት ዳይሬክተሩ።
በአርባ ምንጭ ከተማ እየተገነባ ያለው አዲሱ የማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት ከከተሞችና ከኢንቨስትመንት መስፋፋት ጋር ተያይዞ የሚመጡ የኃይል ጥያቄዎችን በአግባቡ ለማስተናገድ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥርም ተናግረዋል።


እንደ አቶ ገረመው ገለፃ በአካባቢው የግብርና ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች እና ትላልቅ የአገልግሎት ሰጭ ተቋማት እየተስፋፉ ባለበት ወቅት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የማከፋፈያ ጣቢያውን ቀድሞ መገንባቱ የኃይል አቅርቦቱ ከፍላጎት ጋር የተጣጣመ እንድሆን ያስችላል።
ለዚህም የማከፋፈያ ጣቢያው እንደተጠናቀቀ በወቅቱ ኃይል ለማቅረብ እንዲቻል ብሬከሮችን ዝግጁ ከማድረግ ጀምሮ የማሰራጫ መስመር የምሰሶ ተከላ ሥራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
በአካባቢው አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት እንዲኖር ሁለቱ ተቋማት በቅንጅት እንደሚሰሩ አቶ ገረመው አስታውቀዋል።
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”


