በኢትዮ-ኬንያ ኢንተር ኮኔክሽን የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ላይ የችግር ጠቋሚ (fault locater) መሳሪያን ተግባራዊ ለማድረግ በውስጥ አቅም በተከናወነ የማስተካከል ሥራ 60 ሺህ የሚደርስ የአሜሪካ ዶላር ማዳን መቻሉን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።
በተቋሙ የኢንጅነሪንግ ቢዝነስ ዘርፍ ሬዚደንት ኘሮጀክት ሥራ አስኪያጅና በወቅቱ የኢትዮ -ኬንያ ኘሮጀክት ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ ቴዎድሮስ አያሌው እንዳስታወቁት በከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሩ ላይ ችግር ሲፈጠር የሚጠቁመው መሳሪያ ከአራት ዓመታት በላይ ሥራ ሳይሰራ ቆይቷል።

በተደጋጋሚ ተሞክሮ ዉጤታማ ያልሆነውን የችግር ጠቋሚ መሳሪያ የገጠመውን ችግር ለመለየት በተደረጉ ምርመራዎች እና ፍተሻዎች መሳሪያው በግንባታ ወቅት የቴክኒክ ችግር እንዳለበት መረጋገጡን ገልጸዋል።
እንደ ሥራ አስኪያጁ መሳሪያው በአዲስ እንዲተካ ከኘሮጀክቱ ተቋራጭ ጋር መግባባት ላይ ተደርሶ በአዲስ መተካት ቢቻልም አዲሱን መሳሪያ ፈትሾና ሞክሮ ሥራ ለማስጀመር የውጭ ተቋራጭ 60 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ተቋሙን ጠይቋል።
ይሁን እንጅ ከዚህ በፊት የተገኙ ልምዶችን በመጠቀም እና ማንዋሎችን በማንበብ በተቋሙ በውስጥ አቅም ማስተካከል እንደሚቻል ተወስኖ ወደ ሥራ መገባቱን ሥራ አስኪያጁ አስረድተዋል።
በመስመሩ ላይ ኃይል ሳይቋረጥ ሠው ሰራሽ ስህተቶቸን በመፍጠር ችግሩ የተፈጠረበትን ትክክለኛ ቦታ ለማወቅ በድሮን የታገዘ ሙከራ ተደርጎ ውጤታማ በመሆኑ መሳሪያውን ሥራ ማስጀመር እንደተቻለ ነው የገለጹት።
የወላይታ ሶዶ ኮንቨርተር ጣቢያ ኃላፊ አቶ ሀብታሙ ግርማ በበኩላቸው ከዚህ በፊት መሳሪው ተግባራዊ ባለመደረጉ በመስመሩ ላይ ችግር ሲያጋጥም ትክክለኛ ቦታውን ለማግኘት ከሶዶ እስከ ኬንያ ያለውን 1 ሺህ 40 ኪሎ ሜትር መፈተሽ ግዴታ እንደነበር አስታውሰዋል።
ይህም የተፈጠረውን ችግር በፍጥነት ለመለየት የማያስችልና ለመጠገን ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ በኦኘሬሽን ሥራው ላይ ጫና ከማሳደሩም ባሻገር ከኃይል ኤክስፖርት የሚገኘውን ገቢ ላይ የራሱ የሆነ ጫና ያሳድር እንደነበረ አስረድተዋል።
የፍተሻ መሳሪያው ተግባራዊ መደረጉ ቀደም ሲል በመስመሩ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ሙሉ በሙሉ የሚፈታና የጣቢያውን ኃይል የመስጠት ዝግጁነት የሚያጠናክር እንዲሁም ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለውን የኤሌክትሪክ ኃይል ትስስር የማሚያጠናክር ሚናው ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”


