የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮቹ የፍተሻ እና ሙከራ ሥራ ተጠናቀቀ

የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮቹ የፍተሻ እና ሙከራ ሥራ ተጠናቀቀ

የብሔራዊ ኤሌክትሪክ ደቡባዊ ግሪድ ማስፋፊያ ፕሮጀክት አካል የሆኑት የወላይታ ሶዶ ቁጥር 2 – አርባ ምንጭ ቁጥር 2 ባለ 230 ኪሎ ቮልት እና የአርባ ምንጭ ቁጥር 2 – አርባ ምንጭ ቁጥር 2 ባለ 132 ኪሎ ቮልት የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች የሙከራ እና ፍተሻ ሥራ መጠናቀቁን ፕሮጀክት ጽ/ቤቱ አስታወቀ።

የፕሮጀክቱ ተወካይ ሥራ አስኪያጅ አቶ አንዱዓለም መላኩ እንዳስታወቁት የመስመር ዝርጋታዎቹ አዲስ የተገነቡትን የወላይታ ሶዶ ቁጥር 2 ባለ 230 ኪሎ ቮልት የማስፋፊያ እና የአርባ ምንጭ ሁለተኛ ባለ 230 ኪሎ ቮልት አዲስ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ እንዲሁም የአርባ ምንጭ ቁጥር 1 ባለ 132 ኪሎ ቮልት ማስፋፊያ ግንባታዎችን ለአገልግሎት ዝግጁ ለማድረግ የሚያስችሉ ናቸው።

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ 130 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚሸፍነው የወላይታ ሶዶ ቁጥር 2 – አርባ ምንጭ ቁጥር 2 ባለ 230 ኪሎ ቮልት ጥምር የማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ 381 የኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎች አሉት፡፡

12 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚሸፍነው የአርባ ምንጭ ቁጥር 2 – አርባ ምንጭ ቁጥር 1 ባለ 132 ኪሎ ቮልት የማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ ደግሞ 45 የኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎች እንዳሉት ነው አቶ አንዱዓለም ያብራሩት።

የማስተላለፊያ መስመሮቹ ግንባታ መጠናቀቅ የፍተሻ ሥራው በሚቀጥሉት ቀናት ውስጥ ለሚጠናቀቀው ለአርባ ምንጭ ቁጥር 2 የጂ.አይ.ኤስ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ኤሌክትሪክ ለማቅረብ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ነው ሥራ አስኪያጁ የጠቆሙት።

እንደ አቶ አንዱዓለም ገለፃ የማስተላለፊያ መስመሮቹ በአርባምንጭ ለሚገነባው የተቀናጀ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ እንዲሁም በዙሪያው በሚገኙ አካባቢዎች ይስተዋሉ ለነበሩ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ችግሮች መፍትሔ በመስጠት አስተማማኝ ኃይል ያቀርባሉ።

የወላይታ ሶዶ ቁጥር 2 – አርባ ምንጭ ቁጥር 2 ባለ 230 ኪሎ ቮልት እና የአርባ ምንጭ ቁጥር 2 – አርባ ምንጭ ቁጥር 1 ባለ 132 ኪሎ ቮልት ኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችን በሚቀጥሉት ቀናት አገልግሎት ለማስጀመር እንደሚሰራም ነው የገለፁት።

ይህን ተከትሎም የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮቹ በሚያልፉባቸው በወላይታ ዞን የወላይታ ሶዶ ከተማ ፣ የወላይታ ሶዶ ዙሪያ፣ የሁምቦ እና የኦፋ ወረዳዎች እንዲሁም በጋሞ ዞን የቦረዳ፣ የምዕራብ አባያ፣ የጬንቻ እና የአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳዎች እንዲሁም የብርብር እና የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

ፕሮጀክቶቹ ከደቡብ ኮሪያ የኢምፖርት ኤክስፖርት ባንክ የኢኮኖሚ ልማት ትብብር ፈንድ በብድር ከተገኘ በጀት ውስጥ በ26 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር መገንባታቸውን ገልፀዋል።

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top