የኃይል የማከፋፈያ ጣቢያው የማስፋፊያ ሥራ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ

የኃይል የማከፋፈያ ጣቢያው የማስፋፊያ ሥራ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ

የወላይታ ሶዶ ቁጥር 2 ባለ 400/230 ኪሎ ቮልት ማከፋፈያ ጣቢያ የማስፋፊያ ግንባታ ሥራ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የብሔራዊ ኤሌክትሪክ ደቡባዊ ግሪድ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት አስታወቀ።

የፕሮጀክቱ ተወካይ ሥራ አስኪያጅ አቶ አንዱዓለም መላኩ እንደገለፁት በማከፋፈያ ጣቢያው ተጨማሪ 230 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ ኃይል ማቅረብ የሚያስችል የማስፋፊያ ሥራ በማከናወን በዛሬው ዕለት ለአገልግሎት በቅቷል።

በማስፋፊያ ሥራው እያንዳንዳቸው 250 ሜጋ ቮልት አምፒር የመጫን አቅም ያላቸው ሁለት ትራንስፎርመሮች ተከላ መከናወኑንም ነው የተናገሩት።

እንደ አቶ አንዱዓለም ገለፃ የማስፋፊያ ግንባታው ነባሩን የወላይታ ሶዶ ቁጥር 2 የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ አቅም በ500 ሜጋ ቮልት አምፒር የሚያሳድግና ለአካባቢው የኤሌክትሪክ ፍላጎት ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥ ነው።

የወላይታ ሶዶ ቁጥር 2 የማከፋፈያ ጣቢያ የማስፋፊያ ግንባታ መጠናቀቅ አዲስ እየተገነቡ ለሚገኙት ለአርባ ምንጭ እና ሽግዳን የጂ.አይ.ኤስ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች በቀጥታ ኃይል ለማቅረብ የሚያስችል መሆኑንም ነው ሥራ አስኪያጁ የጠቆሙት።

የማስፋፊያ ሥራው መጠናቀቅ የኦሞ ኩራዝ ስኳር ፋብሪካዎች ከሚጠቀሙት የሸንኮራ አገዳ ተረፈ ምርት ሊመነጭ ከሚችል ከ180 ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል የተወሰነውን በዚሁ የደቡባዊ ግሪድ ኘሮጀክት ግንባታ አካል በሆኑት የሽግዳን እና ቲርጋ የማከፋፈያ ጣቢያዎች አማካኝነት ወደ ብሔራዊ የኃይል ቋት ለማስገባት እንደሚያግዝም አስረድተዋል፡፡

ይህም የኢነርጂ ስብጥሩን ከፍ ከማድረጉም በተጨማሪ በሀገሪቱ ያለውን የኃይል አቅርቦት አቅም የሚያሳድግ ነው ብለዋል፡፡

የወላይታ ሶዶ ቁጥር 2 የማከፋፈያ ጣቢያ የማስፋፊያ ግንባታ ሁለት ባለ 230 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮች ሲኖሩት ይህም በአካባቢው ይስተዋል ለነበረው የኤሌክትሪክ አቅርቦት ችግር መፍትሔ በመስጠት የግሪድ ሥርዓቱን ከማጠናከሩም ባሻገር በወላይታ ሶዶ እና አርባምንጭ ከተሞች እና በዙሪያቸው ለሚገነቡ ኢንዱስትሪዎች አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ ያስችላል፡፡

የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያውን የማስፋፊያ ግንባታ ሃዮሰንግ ሄቪይ ኢንደስትሪስ ኮርፖሬሽን እንዲሁም የማማከር ሥራውን ደግሞ ባዩክሰን ፓወር የተሰኙ የደቡብ ኮሪያ ኩባንያዎች አከናውነውታል።

የወላይታ ሶዶ ቁጥር 2 የማከፋፈያ ጣቢያ የማስፋፊያ ግንባታ ፕሮጀክት ከደቡብ ኮሪያ የኢምፖርት ኤክስፖርት ባንክ የኢኮኖሚ ልማት ትብብር ፈንድ በብድር ከተገኘ የፋይናንስ አቅርቦት ውስጥ በ15 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የተገነባ ነው።

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top