በወላይታ ሶዶ ከተማ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙት ሁለቱ የኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች በሶዶ ከተማ እና በዙሪያው አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት እንዲኖር ማስቻላቸውን የከተማዋ ከንቲባ አስታወቁ።
ከንቲባዋ ወይዘሮ እታገኝ ኃይለማሪያም እንዳስታወቁት ለከተሞች እና ለኢንቨስትመንት መስፋፋት፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ እንዲሁም ለቱሪዝም ዕድገት የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ከፍተኛ ድርሻ አለው።

በከተማዋ የሚገኙ ማከፋፈያ ጣቢያዎች ለኢንዱስትሪዎች እና ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት በቂ ኃይል እያቀረቡ እንደሚገኙ በማንሳት የኃይል አቅርቦቱ ለከተማዋ መስፋፋት፣ በኢንቨስትመንት፣ በአገልግሎት አሰጣጥ እና በነዋሪዎች የዕለት ተዕለት ኑሮ ላይ አዎንታዊ ለውጥ እያመጣ መሆኑንም ተናግረዋል።
ማከፋፈያ ጣቢያዎቹ የከተማዋን የኃይል አቅርቦት ችግር በዘላቂነት ከመፍታት ባለፈ ለተለያዩ የልማት ሥራዎች መፋጠን ጉልህ ድርሻ እንዳላቸውም አስረድተዋል።
ሶዶ ከተማ የሰባት በሮች መገናኛ እና ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ የሚካሄድባት መሆኗን ያነሱት ከንቲባዋ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል በመኖሩ በከተማዋ ያለው የኢንቨስትመንት ፍሰት ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ መጥቷል ብለዋል፡፡
የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦን ጨምሮ የተለያዩ የማህበራዊ አገልግሎቶችን ለህብረተሰቡ በቀላሉና በተገቢው መንገድ ለማዳረስ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ እንደምገኝም አብራርተዋል ።
የኃይል አቅርቦቱ መሻሻል የከተማዋ ነዋሪ ከባህላዊ የኃይል ምንጮች ተላቆ የኑሮ ዘይቤው በኤሌክትሪክ ኃይል እንዲመሠረት ማድረጉንና ይህም ጤናማ እና የተሻለ የአኗኗር ዘይቤ የሚከተል ማህበረሰብ በመፍጠር በኩል የራሱ የሆነ አስተዋፅኦ እንዳለው ነው ያስረዱት።


በከተማዋ በሆቴል እና ቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶች በበኩላቸው አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት በማግኘታቸው ሥራቸውን ውጤታማ እንዳደረገላቸው አስረድተዋል።
የሌዊ ሪዞርት ወላይታ ሶዶ ሥራ አስኪያጅ አቶ ደመላሽ ተስፋዬ እንደገለጹት የማከፋፈያ ጣቢያዎቹ በአቅራቢያቸው በመገኘታቸው ፍላጎታቸውን የሚያሟላ በቂ ኃይል እንዲያገኙ ማድረጉንና ይህም ጥራት ያለው አገልግሎት በመስጠት የደንበኞችን እርካታ ለማሳደግ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።
በተጨማሪም የኤሌክትሪክ ሥራቸውን ቀጣይነት ባለው መልኩ እንዲያከናውኑ በማስቻል በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸዉን ገልጸዋል።
የኃይሌ ሆቴልና ሪዞርት ወላይታ ሶዶ የሰው ሀብት ሥራ አስኪያጅ አቶ ወንደሰን ኦልቀባ በበኩላቸው የኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎቹ በቅርበት በመገኘታቸው ሆቴሉ አስተማማኝና ደንበኞችን ያማከለ ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጥ ትልቅ አቅም እንደፈጠረ አስታውቀዋል።
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”


