የማከፋፈያ ጣቢያውን አቅም የማሳደግ ሥራ እየተከናወነ ነው

የማከፋፈያ ጣቢያውን አቅም የማሳደግ ሥራ እየተከናወነ ነው

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በሰሜን ምዕራብ ሪጅን ሥር የሚገኘውን የአዘዞ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ አቅም ለማሳደግ የሚያስችል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ አስታወቁ።

ሥራ አስኪያጁ አቶ ይገርማል ማሩ እንደገለፁት ጣቢያው አገልግሎት መስጠት ከጀመረበት 1995 ዓ.ም. ጀምሮ የአካባቢውን የኃይል ፍላጎት በማሟላት ረገድ ከፍተኛ ሚና ሲጫወት ቆይቷል፡፡

በአሁኑ ወቅት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያውን የኦፕሬሽን አቅም ለማሳደግ በባለ 33 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮች የዘመናዊ መቆጣጠሪያ ብሬከር ቅየራ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ነባሩ ባለ 33 ኪሎ ቮልት መቆጣጠሪያ ረጅም ዘመን በማገልገሉ በተደጋጋሚ የኃይል መቆራረጥ ያጋጥም እንደነበር የጠቀሱት ሥራ አስኪያጁ አዲሱ ዘመናዊ ብሬከር የኃይል መቆራረጡን በማስወገድና የቁጥጥር ሥርዓቱን በማዘመን የጣቢያውን ደህንነት እንደሚያስጠብቅ አንስተዋል።

እንደ አቶ ይገርማል ገለፃ ቀደም ሲል የነበረው መቆጣጠሪያ ችግሮች ሲያጋጥሙ የጥገና ሥራ ለማከናወን ረዘም ያለ ጊዜ ይወስድ ነበር።

የመቆጣጠሪያው መቀየር የኃይል መቆራረጥንና በጥገና ሥራዎች ላይ ያጋጥሙ የነበሩ ችግሮችን በመቅረፍ የኦፕሬሽን ሥርዓቱን ለማቀላጠፍ እንደሚረዳም ነው ያብራሩት።

ይህም የጣቢያውን አቅም በማሳደግ የኃይል አቅርቦቱን አስተማማኝነት ለመጨመር እንደሚያግዝ ጠቅሰው ከደንበኞች ለሚነሱ የኃይል ፍላጎት ጥያቄዎች አስተማማኝ ምላሽ ለመስጠት ሚናው የጎላ እንደሆነም ገልፀዋል።

የብሬከር ቅየራው አሁን ላይ ከ80 በመቶ በላይ አፈፃፀም ማስመዝገቡን የጠቀሱት አቶ ይገርማል የማሻሻያ ሥራው ሲጠናቀቅ የጣቢያውን ኃይል የማቅረብ አቅም አስተማማኝና የተቀላጠፈ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።

ማከፋፈያ ጣቢያው 63፣ 40 እና 31 ነጥብ 5 ሜጋ ቮልት አምፔር መጠን ያላቸው ሦስት ትራንስፎርመሮች ያሉት ሲሆን ትራንፎርመሮቹ እስከ 200 ሜጋ ዋት ኃይል የመጫን አቅም እንዳላቸውም ነው የገለፁት፡፡

የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያው ሁለት ባለ 230፣ አንድ ባለ 66፣ ስድስት ባለ 33 እና አስራ ሁለት ባለ 15 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮች አሉት።

ጣቢያው ከባህርዳር ማከፋፈያ ጣቢያ ኃይል ተቀብሎ በሃያ አንድ የ230፣ 66፣ 33 እና 15 ኪሎ ቮልት መስመሮች ለጎንደር፣ መተማ፣ ሳንጃ፣ አርባያ፣ ደልጊ፣ ጭልጋ፣ ጎርጎራ፣ ማክሰኚት እንዲሁም ለኢንዱስትሪዎች፣ ለአንገረብ ቁጥር 1 የንፁህ መጠጥ ውሃ፣ ለጎንደር ቁጥር 1 ማከፋፈያ ጣቢያ፣ ለዳሽን ቢራ ፋብሪካ፣ ለጎንደር ዩኒቨርሲቲ እና በዙሪያው ለሚገኙ አካባቢዎች ኃይል እያቀረበ ይገኛል፡፡

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top