በኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ዘመናዊ የአሰራር ሥርዓቶችን ለጥገና ሥራዎች ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የጀነሬሽን ቢዝነስ ዘርፍ አስታወቀ።
በዘርፉ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ኤፍሬም ወልደኪዳን የተመራ የባለሙያዎች ቡድን በአዳማ አንድ እና ሁለት የንፋስ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች የመስክ ምልከታ አድርጓል።


የመስክ ምልከታው ተቋሙ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎቹን ውጤታማነት፣ ደህንነት እና ዘመናዊ የአሰራር ሥርዓት ለማሳደግ የጀመረው ስትራቴጂካዊ የክትትል አካል መሆኑ ተገልጿል።
በዚሁ ወቅት ኢንጂነር ኤፍሬም ወልደኪዳን እንደተናገሩት ጣቢያዎቹ በሀገራዊ የኃይል አቅርቦት መረብ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው ናቸው።
በተቋሙ ተግባራዊ የተደረገው ሳፕ የተሰኘውን ዘመናዊ አሰራር ሥርዓት የኃይል ማመንጫ ጣቢዎች የጥገና ሥራዎችን በሚያከናውኑበት ወቅት እንደ ግብዓት መጠቀም እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
በጣቢያዎቹ የሥራ ላይ ደህንነት ከአሰራር ሥርዓት ባለፈ እንደ እሴትና ባህል ሊወሰድ እንደሚገባ ገልፀው አመራሩም ለሠራተኛው ደህንነት መጠበቅ አርዓያ መሆን እንዳለበት አፅንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።
በጣቢያዎቹ ከሥራ ላይ ደህንነት ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ መዘናጋቶችን ለመቅረፍ የዜሮ መቻቻል (Zero Tolerance) መመሪያን ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸውም ነው ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚው የገለፁት፡፡
ጣቢያዎቹ በዘመናዊ የአሰራር ሥርዓት አጠቃቀም፣ በአስተዳደር እና በሥራ ላይ ደህንነት ጉዳዮች ላይ የታዩ ክፍተቶችን በአስቸኳይ በመፍታት ወደ ተግባር እንዲሸጋገሩ መመሪያም ሰጥተዋል፡፡
ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚው ከጣቢያዎቹ ሥራ አስኪያጆች እና የጥገና ባለሙያዎች ጋር በመሆን የንፋስ ተርባይኖችን እና የመቆጣጠሪያ ክፍሎችን እንዲሁም የጥገና ወርክሾፖችን ጎብኝተዋል።
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”


