የታሪፍ ድርድር ማዕቀፍን ለማዘመን የሚያስችል የጥናት ማስጀመሪያ ፕሮግራም ተካሄደ

የታሪፍ ድርድር ማዕቀፍን ለማዘመን የሚያስችል የጥናት ማስጀመሪያ ፕሮግራም ተካሄደ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከደቡብ ኮሪያ ሪፐብሊክ መንግሥት ጋር የኤሌክትሪክ ታሪፍ ድርድር ማዕቀፍን ለማዘመን የሚያስችል የጥናት ማስጀመሪያ መርሀ ግብር በዛሬው ዕለት አካሂዷል፡፡

በጥናት ማስጀመሪያ መርሀ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ ኢትዮጵያና ደቡብ ኮሪያ የኃይል ልማት ዘርፍን ለማሳደግና ለማዘመን በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ በትብብር ሲሰሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከታዳሽ ኃይል ኤሌክትሪክ ለማመንጨት የሚያስችል ሰፊ ሀብት ቢኖራትም አሁን ላይ የኃይል ተደራሽነት ሽፋኑ 54 በመቶ ብቻ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ተቋሙ የፋይናንስ አቅሙን በማጠናከር ሀገሪቱ ያላትን እምቅ የታዳሽ ኃይል ክምችት በመጠቀም ሽፋኑን ለማሳደግ ከታሪፍ ማሻሻያ ጋር ተያይዞ ያሉ አሰራሮችን ለማዘመን ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡

እንደ ኢንጂነር አሸብር ገለፃ ፕሮግራሙ ደቡብ ኮሪያ ከታሪፍ ድርድር ማዕቀፍ ጋር ያላትን የዳበረ ተሞክሮ በመውሰድ በሥራ ላይ ያሉ አሰራሮችን ለማዘመን ዕድል የሚፈጥር ነው፡፡

ትብብሩ የዕውቀት ሽግግርን ባረጋገጠ አግባብ ጥናት በማካሄድ አቅጣጫ ከማመላከት ባለፈ ደቡብ ኮሪያውያን ባለሃብቶች በኃይል ልማት ዘርፉ እንዲሳተፉ በር ይከፍታል የሚል እምነት እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡

ፕሮግራሙ በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ወደ ትግበራ እንዲገባ ተቋሙ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በአግባቡ እንደሚወጣም ነው ያረጋገጡት፡፡

በኢትዮጵያ የደቡብ ኮሪያ አምባሳደር ሚስተር ጀንግ ካንግ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ወታደሮች በኮሪያ ጦርነት ወቅት ከደቡብ ኮሪያ ሕዝብ ጎን በመሰለፍ ለሰላምና ነፃነት መስፈን የከፈሉት መስዋዕትነት በታሪክ ሲዘከር የሚኖርና የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ይበልጥ ያስተሳሰረ ነው ብለዋል፡፡

የሀገራቱን ታሪካዊ ግንኙነት ለማጠናከር የኃይል ልማት ዘርፉን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች በርካታ ሥራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን አንስተዋል፡፡

የደቡብ ኮሪያ መንግሥትና በአዲስ አበባ የሚገኘው ኢምባሲ የዕውቀት ሽግግርን ለማድረግ የሚደረገውን ጥናት ጨምሮ የኃይል ልማት ዘርፉን ለማዘመን የሚያስችል ድጋፍ ለማድረግ ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኢትዮ-ፓወር አካዳሚ ዳይሬክተር ወንድወሰን ካሳ (ዶ/ር) በደቡብ ኮሪያ መንግሥት በሚደገፈው የዕውቀት ሽግግር ፕሮግራም ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከቀረቡ ከ400 በላይ ፕሮጀክቶች መካከል ኢትዮጵያ ያቀረበችው የኤሌክትሪክ ታሪፍ ድርድር ማዕቀፍን የማዘመን ፕሮጀክት አሸናፊ በመሆን ዕድሉ መገኘቱን ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም በደቡብ ኮሪያ መንግሥት የባለሙያ ድጋፍ በማድረግ የሚከናወነው የአሰራር ማዘመን ጥናት የዕውቀት ሽግግርን ከማረጋገጥ ባለፈ የተቋሙን ባለሙያዎች አቅም በመገንባት በኩል የጎላ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡

የኤሌክትሪክ ታሪፍ ድርድር ማዕቀፍ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን በማድረግ የተቋሙን የፋይናንስ ቁመና በማጎልበት፣ የግል ኢንቨስትመንቶችን በማበረታታት እና ስጋትን በመቀነስ ተልዕኮውን እንዲያሳካ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ይኖረዋል ብለዋል፡፡

የደቡብ ኮሪያ የዕውቀት ሽግግር ፕሮግራም ከፍተኛ አማካሪ ሚስተር ሲየንግል ቼል ሊ በበኩላቸው ጥናቱን በአጭር ጊዜ ውስጥ በማጠናቀቅ የኤሌክትሪክ ታሪፍ ድርድር ማዕቀፉን ለማዘመን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡

ፕሮግራሙን በማስተግበር ሂደት የደቡብ ኮሪያ የንግድና ኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን ኤጀንሲ የአዲስ አበባ ቢሮ ዋነኛ ሚና እንደሚኖረው በዳይሬክተር ጀኔራሉ ሚስተር ጂንሶክ ፓርክ በኩል ተገልጿል፡፡

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top