የጥበቃ ሠራተኞች ሙያዊ ሥነ-ምግባርን በተላበሰ መልኩ የተቋሙን ደህንነት ማስጠበቅ እንዳለባቸው ተገለፀ

የጥበቃ ሠራተኞች ሙያዊ ሥነ-ምግባርን በተላበሰ መልኩ የተቋሙን ደህንነት ማስጠበቅ እንዳለባቸው ተገለፀ


የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በኤጀንሲ በኩል የተቀጠሩ አዳዲስ የጥበቃ ሠራተኞችን አቅም ለማሳደግ እና የተቋሙን ደህንነት ለማስጠበቅ ያለመ የሥራ ማስጀመሪያ ሥልጠና በዛሬው ዕለት ሰጥቷል።

በሥልጠናው ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት በተቋሙ የዋና ሥራ አስፈፃሚ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሙላት ገዛኸኝ ሥልጠናው የጥበቃ ሠራተኞቹ ከዚህ ቀደም የሚያውቁትን ልምድ እንዲያሳድጉና አዳዲስ አሰራሮችን እንዲቀስሙ ትልቅ እገዛ ያደርጋል ብለዋል፡፡

በተቋሙ የኃይል መሠረተ ልማት ደህንነት፣ ክትትልና ቁጥጥር መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ከሊል ሽፋ እንደገለፁት የተቋሙን ንብረት መጠበቅና መንከባከብ ለድርጅቱ ህልውና ወሳኝ በመሆኑ የጥበቃ ሠራተኞችን በዕውቀት ማብቃት አማራጭ የሌለው ተግባር ነው።

ከኢፌዴሪ የመከላከያ ሚኒስቴር ተጋብዘው በመጡት ኮሎኔል ለገሰ ስዩም “የመረጃ ሚና በተቋም ጥበቃ” በሚል ርዕስ ሥልጠና የተሰጠ ሲሆን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሀገሪቱ ግዙፍ ሀብት የሚገኝበት ተቋም በመሆኑ ልዩ ጥበቃና ጥንቃቄ እንደሚያስፈልገው አፅንዖት ሰጥተዋል።

የተቋም ጥበቃና ደህንነት የጋራ ሥራ መሆኑን በመጥቀስ ሠራተኞች ፍተሻ በሚያደርጉበት ወቅት ከደንበኞች ጋር ያላቸውን ግንኙነት በክብርና ሙያዊ ሥነ-ምግባርን በተላበሰ መልኩ ሊያከናውኑ እንደሚገባም አሳስበዋል።

ሥልጠናው የጥበቃ ሠራተኞቹ በስራ ገበታቸው ላይ ሊያጋጥሟቸው የሚችሉ ችግሮችን መቆጣጠር በሚችሉባቸው መንገዶች፣ በስርቆት ሙከራ መከላከያ ዘዴዎች እና የተለያዩ ወንጀሎችን አስቀድሞ በመቆጣጠር ስልቶች እንዲሁም ወደ ስምሪት ሲገቡ ሊከተሏቸው ስለሚገቡ አቅጣጫዎችና ደንቦች ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡

Scroll to Top