ፕሮጀክቱ በአማካይ ከ400 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል 

ፕሮጀክቱ በአማካይ ከ400 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል 

የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በአማካኝ ከ400 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ጊዜያዊና ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠሩን የፕሮጀክቱ የሳይት ሥራ አስኪያጅ ገለጹ።

ሥራ አስኪያጁ አቶ ፈቃዱ አብርሃም እንደገለፁት ፕሮጀክቱ 29 የንፋስ ማማዎች ተከላን፣ 230 ኪሎ ቮልት ማከፋፍያ ጣቢያን እና 38 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የባለ 33 ኪሎ ቮልት የማስተላለፊያ መስመር ግንባታ ሥራዎችን ያጠቃልላል።

ከሥራ ተቋራጩ ጋር በተደረገው ስምምነት መሰረት ከፕሮጀክቱ እስከ 25 ኪሎ ሜትር ርቀት ያሉ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ቅድሚያ በመስጠት የአካባቢውን ነዋሪዎች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡

እስካሁን ባለው የፕሮጀክቱ ሂደት በአማካይ ከ400 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠሩንና አብዛኛው ተጠቃሚ የአካባቢው ወጣቶች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል ወጣት ቶሎሳ ሮባ እንደገለፀው በፕሮጀክቱ ሥራ ከመጀመሩ በፊት ቋሚ ሥራ ስላልነበረው በሚያገኘው ገቢ ከራሱ አልፎ ቤተሰብን ለማስተዳደር ትልቅ ፈተና ሆኖበት ነበር።

በፕሮጀክቱ በተፈጠረለት የሥራ ዕድል ላለፉት 2 ዓመታት መስራቱንና በዚህም እሱን ጨምሮ ሦስት ቤተሰቦቹን ለማስተዳደር የሚያስችል የተሻለ ገቢ ለማግኘት እንዳስቻለው ተናግሯል፡፡

ሌላኛዋ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ወጣት ሙሉ ተካ በበኩሏ በፕሮጀክቱ ሥራ ከመጀመሯ በፊት እሷንና ቤተሰቧን ለማስተዳደር አረብ ሀገር ሄዳ ለመስራት ተገዳ እንደነበረ አንስታለች፡፡

ፕሮጀክቱ በትውልድ ቀየዋ ሥራ ከጀመረ ካለፉት 3 ዓመታት ወዲህ ግን በፕሮጀክቱ ተቀጥራ ቤተሰቧን እያስተዳደረችና ልጆቿን እያስተማረች መሆኑን ገልጻለች፡፡

ፕሮጀክቱ ለአካባቢው ማህበረሰብ የሥራ ዕድል ከመፍጠሩም ባለፈ ሲጠናቀቅ አስተማማኝ ኃይል እንዲኖር በማድረግ ኢኮኖሚያዊ እድገትን የሚያፋጥኑ ፕሮጀክቶች እንዲከፈቱ ያግዛል፡፡

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top