የማመንጫ ጣቢያውን ደህንነት ለማስጠበቅ የአካባቢው መስተዳድር አካላት ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

የማመንጫ ጣቢያውን ደህንነት ለማስጠበቅ የአካባቢው መስተዳድር አካላት ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

የመልካ ዋከና የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያን ደህንነት ለማስጠበቅ የአካባቢው መስተዳድር አካላት ሚናቸውን እንዲወጡ  ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጠየቀ።

ተቋሙ የጣቢያውን ደህንነት ማስጠበቅ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከኦሮሚያ ክልል፣ ከምዕራብ አርሲ ዞንና ወረዳዎች ከተውጣጡ የመስተዳድር አካላት ጋር በሻሸመኔ ከተማ ውይይት አካሂዷል፡፡

በውይይቱ ላይ የተቋሙ የኮርፖሬት ገቨርናንስ እና ኮምፒሊያንስ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዱጉማ ነዳ እንደገለፁት የመልካ ዋከና የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ላለፉት 37 ዓመታት አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የገጠሙት ፈተናዎች በጣቢያው የኦፕሬሽን ሥራ እና ደህንነት ላይ አደጋ እየደቀኑ ነው፡፡

በበጋ ወራት ውሃ በሚቀንስበት ወቅት የግድቡን ጥብቅ ወሰን በማለፍ በሚከናወን የእርሻ ሥራ ምክንያት ግድቡ በከፍተኛ ሁኔታ በደለል እንዲሞላ ከማድረጉም በላይ የግብርና ተረፈ ምረቶች ወደ ጣቢያው እየገቡ ውሃ ወደ ኃይል ማመንጫ ቤት እንዳያልፍ እየገደቡ ነው ብለዋል።

እንደ አቶ ደጉማ ገለፃ ተረፈ ምርቶቹ የማቀዝቀዣ መስመሮችን (cooling system) በመዝጋት በከፍተኛ ሙቀት ማሽኖቹ የኤሌክትሪክ ኃይል እንዳያመነጩ በማድረግ በጣቢያው የኦፕሬሽን ሥራ ላይ እንቅፋት ፈጥረዋል፡፡

የምዕራብ አርሲ ዞንና የአዳባ ወረዳ የመስተዳድር አካላት የኃይል ማመንጫ ጣቢያውን ሀገራዊ ፋይዳ ከግምት ውስጥ በማስገባት የይዞታ ማረጋገጫ የሚያገኝበትን ሁኔታ እንዲያመቻቹና ለአካባቢው ሕብረተሰብም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን በማከናወን ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡

የመልካ ዋከና ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ቴዎድሮስ በቀለ በበኩላቸው በግድቡ ጥብቅ ወሰን ውስጥ በሚከናወን የእርሻ ሥራ ምክንያት እየደረሰ ያለውን ጉዳት፣ ከውሃ አጠቃቀም፣ ከይዞታ ማረጋገጫ እና ከወሰን ማስከበር ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮችን በተመለከተ ለውይይት መነሻ የሚሆን ጽሁፍ አቅርበዋል፡፡

በመልካ ዋከና ግድብ ዙሪያ አራት የመንግስት እርሻዎች እንደሚገኙ የጠቀሱት ሥራ አስኪያጁ ከነዚህም መካከል የግድቡን ጥብቅ ወሰን በማለፍ የይዞታ ማረጋገጫ ጭምር ወስደው የእርሻ ሥራ የሚያከናወኑ መኖራቸውንና ይህም የጣቢያውን ደህንነት አደጋ ላይ መጣሉን ገልፀዋል፡፡

ጣቢያው የይዞታ ማረጋገጫ ማግኘት ባለመቻሉ ጥብቅ ወሰኑን በማለፍ ቤት መስራት፣ አጥር ማጠር፣ እርሻ ማረስ እና እንስሳት የማሰማራት ችግሮች እየተፈጠሩ በመሆኑ የወሰን ማስከበር ሥራውን አዳጋች እያደረገው መምጣቱን ጠቅሰዋል፡፡

የኦሮሚያ ገጠር ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ደስታ ነጊሶ በበኩላቸው የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችን ደህንነት መጠበቅ የጎረቤት ሀገራትን በኃይል ለማስተሳሰር የሚደረገውን ጥረት ማገዝ ነው ብለዋል፡፡

ይህን ከግምት በማስገባትም በመልካ ዋከና የኃይል ማመንጫ ጣቢያ ላይ የተከሰቱ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ የባለሙያዎች ቡድን ተዋቅሮ በአጭር ጊዜ ወደ ሥራ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ጣቢያውን ለተጨማሪ የደህንነት አደጋ ሊዳርጉ የሚችሉ ማናቸውም እንቅስቃሴዎች እንዲቆሙ እንዲሁም በግድቡ ዙሪያ ሲሰሩ የነበሩ የተፋሰስ ሥራዎች መልሶ ለማስጀመር ለዞንና የወረዳ መስተዳድር አካላት አቅጣጫ መሰጠቱንም ጠቁመዋል።

በክልሉ የሚገኙ ሁሉም የኃይል ማመንጫዎች የይዞታ ማረጋገጫ እንዲያገኙ ለማድረግ ክልሉ ከተቋሙ ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።

በቀረበው ጽሁፍ ላይ ውይይት የተደረገ ሲሆን የማመንጫ ጣቢያው መኖር ከተሞች እንዲስፋፉ፣ የመብራትና ውሃ አቅርቦት እንዲኖር እንዲሁም በአቅራቢያቸው ትምህርት ቤት እንዲከፈት በማድረግ በኩል ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው የዞንና የወረዳ መስተዳድር አካላት አንስተዋል።

ሕብረተሰቡን በማወያየት የማመንጫ ጣቢያውን ደህንነት ለማስጠበቅ ከተቋሙ ጋር ተቀራርበው ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

በ1980 ዓ.ም አገልግሎት መስጠት የጀመረው የመልካ ዋከና የውኃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ 153 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም አለው፡፡

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top