ተቋማቱ በጋራ ለመስራት በሚያስችሏቸው የሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ውይይት አካሄዱ

ተቋማቱ በጋራ ለመስራት በሚያስችሏቸው የሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ውይይት አካሄዱ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በጋራ መስራት በሚችሉባቸው የሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡

ምክክሩ ሁለቱ ተቋማት ከዚህ ቀደም በጋራ ያከናወኗቸውን ሥራዎች ለመገምገምና ቀጣይ የሥራ ግንኙነቶች በሚጠናከሩበት ሁኔታ ላይ ያለመ ነው።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ በውይይቱ ወቅት እንደተናገሩት ተቋሙ የኃይል ልማት ዘርፉን ለማሳደግ የሚያስችሉ የተለያዩ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ላይ ይገኛል።

ተቋሙ በሚያከናውናቸው የኃይል መሠረተ ልማት ግንባታዎች ላይ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት አሻራ የጎላ መሆኑንም አንስተዋል።

እንደ ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገለፃ ተቋማቱ የዘረጉትን የኢ.አር.ፒ ቴክኖሎጂ በመጠቀም የመረጃ ልውውጥ ሥርዓታቸውን ማሳለጥ ይገባቸዋል።

ከዚህ ቀደም ከአሰራር ሥርዓትና አገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዘው ይነሱ የነበሩ ችግሮች ዳግም እንዳይከሰቱ ለማድረግ ከሁለቱ ተቋማት የተውጣጣ ቡድን በማዋቀር መስራት እንደሚገባም አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የጀነሬሽን ቢዝነስ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ኤፍሬም ወ/ኪዳን በበኩላቸው የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት አሁን ለደረሰበት የግንባታ ምዕራፍ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት አስተዋፅዖ ከፍተኛ ነው ብለዋል።

በኃይል ልማት ዘርፍ እየተከናወኑ የሚገኙ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት ተቋሙ ቅድሚያ ሰጥቶ እገዛ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

ተቋማቱ በፋይናንስ የመረጃ ልውውጥ ላይ ያላቸውን የአሰራር ቅልጥፍና ማዘመን እንደሚጠበቅባቸው የጠቀሱት ደግሞ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮርፖሬት ፋይናንስና ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ደመረ አሰፋ ናቸው።

በኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የሺፒንግ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ካፒቴን ወንድወሰን ካሳ የተቋማቸውን አሁናዊ ገፅታ አስመልክተው ገለፃ አድርገዋል።

ተቋማቸው በሀገራዊ የኃይል መሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ላይ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ በመሆኑ ኩራት እንደሚሰማቸውም ነው የተናገሩት።

ከኮንቴነር ኪራይ፣ ከደረቅ ወደብ አጠቃቀም እና ከፋይናንስ እንዲሁም ከአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ጋር ተያይዘው ለሚነሱ ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት ተቋማቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተቀራርበው መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ የጭነትና አስተላላፊነት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሻረው ከበደ በበኩላቸው ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት የግንባታ ዕቃዎች በወቅቱ የሚቀርቡ ከሆነ የማጓጓዝ ሥራዎችን በፍጥነት ለማከናወን ተቋማቸው ዝግጁ መሆኑን ገልፀዋል።

በውይይቱ ላይ የሁለቱ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top