የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የመልካ ዋከና የውሃ የኃይል ማመንጫ ጣቢያን ደህንነት ማስጠበቅ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከኦሮሚያ ክልል እና ከምዕራብ አርሲ የዞን የመስተዳድር አካላት ጋር በሻሸመኔ ከተማ ውይይት ማካሄድ ጀምሯል።
በተቋሙ የኮርፖሬት ገቨርናንስ እና ኮምፒሊያንስ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ደጉማ ነዳ እንደገለጹት ውይይቱ በግድቡ ጥብቅ ወሰን ውስጥ በሚከናወን እርሻ ምክንያት በግድቡ ላይ እየደረሰ ባለው ጉዳት፣ ከግድብ ውሃ አጠቃቀም፣ ከይዞታ ማረጋገጫ እና ከወሰን ማስከበር ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት ያለመ ነው።
የማመንጫ ጣቢያው የይዞታ ማረጋገጫ ባለማግኘቱ በበጋ ወራት የጣቢያውን ጥብቅ ወሰን በማለፍ እርሻዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህም ጣቢያው በደለል እንዲሞላ ከማድረጉም በላይ የግብርና ተረፈ ምረቱ ወደ ጣቢያው በመግባት ውሃ ወደ ተርባይኖቹ እንዳያልፍ በማድረግ የጣቢያውን የኦፕሬሽን ሥራ እና ደህንነት ላይ ስጋት መደቀኑን ተናግረዋል።
ተቋሙ በጣቢያው ላይ እያጋጠሙት ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ከአካባቢው የመስተዳድር አካላት እና ማህበረሰቡ ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ዝግጁ መሆኑንም አብራርተዋል።
ከዚሁ በተጨማሪም ተቋሙ እያከናወናቸው ባሉ የማህበራዊ ኃላፊነት ሥራዎች እና ለአካባቢው ማህበረሰብ በሠራቸው የልማት ሥራዎች ዙሪያ ውይይት እየተደረገ ነው።
በውይይቱ ላይ የተቋሙና የጣቢያው ኃላፊዎችን ጨምሮ የኦሮሚያ የገጠር ልማት ክላስተር፣ የዞንና ወረዳ መስተዳድር አካላት እየተሳተፉ ይገኛል።
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”



