በ2017 የመጀመሪያ ግማሽ በጀት ዓመት በሰባት ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ ዘመናዊ ስዊች ጊር ወይም መቆጣጠሪያ የመቀየር ሥራ መከናወኑን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን ዘርፍ ገለጸ፡፡
በዘርፉ የሪጅኖች ማስተባበሪያ መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ጋሻው እንድሪያስ እንደገለፁት በ2017 በጀት ዓመት የ37 ማከፋፈያ ጣቢያዎች የመቆጣጠሪያ ሥርዓት በዘመናዊ የመቆጣጠሪያ ለመቀየር ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡
በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት የሰባት ማከፋፈያ ጣቢያዎችን የባለ 15 እና 33 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮች በዘመናዊ መቆጣጠሪያዎች የመቀየር ሥራ ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀ ሲሆን በ21 ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ ደግሞ የሲቪል ሥራና የዕቃ ማጓጓዝ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በአሸጎዳ፣ በድሬድዋ ሦስት፣ በጅጅጋ፣ በባህርዳር ሁለት፣ በዲላ እና በጋሸና ማከፋፈያ ጣቢያዎች በግማሽ በጀት ዓመቱ የቅየራ ሥራው መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡
የሚቀየረው ስዊች ጊር በማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ ያጋጥም የነበረውን የጥገና ስራ በማስቀረት እና የኃይል መቆራረጥን በመቀነስ የኃይል አቅርቦቱን አስተማማኝነት እንደሚያሳድግ ገልጸዋል፡፡
የመቆጣጠሪያ ብሬከሩ ሙሉ በሙሉ ዝግ ሆኖ የሚሰራ በመሆኑ ከአቧራ፣ ከእርጥበት ብሎም ከውጫዊ አየር ተጠብቆ ረጅም ጊዜ እንደሚያገለግል ገልጸው ከአሁን ቀደም ኋላ ቀር በሆነ ቴክኖሎጂ ሲሰራበት የነበረውን አሰራር በማስወገድ የማከፋፈያ ጣቢያዎችን አቅም የሚያሳድግ እና አሰራሩን የሚያዘምን ነው ብለዋል፡፡
በተቋሙ የማከፋፈያ ጣቢያዎች የጥገና ባለሙያና የማዘመን ሥራው አስተባባሪ አቶ ሚሊዮን በለጠ በበኩላቸው የስዊች ጊር ቅየራው በጊዜያዊ ሌሎች የመቆጣጠሪያ ሥርዓት በመዘርጋት ኃይል ሳይቋረጥ እየተከናወነ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
የቅየራ ስራው በተቋሙ ባለሙያዎች መከናወኑን የገለጹት አቶ ሚሊዮን ይህም የባለሙያዎችን አቅም ከማሳደግ በተጨማሪ ለውጭ ኩባንያ ይከፈል የነበረውን ወጭ ከ50 በመቶ በላይ ያስቀረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አስተባባሪው እንዳሉት የዘመናዊ መቆጣጠሪ ብሬከሩን ከሚያቀርበው ኩባንያ ጋር በመተባበር የባለሙያዎች አቅም ግንባታ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል፡፡
ብሬከሮች በሚቀየሩባቸው ማከፋፈያ ጣቢዎች አካባቢ የክሬን አገልግሎት የሚሰጡ ድጅቶች አለመኖር፣ ለሲቪል ግንባታ የሚያገለግሉ ግብዓቶች እጥረት እና ዕቃዎችን ወደ ጣቢያ ለማድረስ የመንገድ ችግር በሥራው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደራቸውን ገልጸዋል፡፡
ተቋሙ በሦስት ምዕራፎች በ75 ማከፋፈያ ጣቢዎች ላይ የማዘመን ሥራ ለማከናወን አቅዶ እየሰራ ሲሆን እስከ አሁን የ25 ማከፋፈያ ጣቢዎች ሥራ ተጠናቋል፡፡
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”





