የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ግንባታ 78 ነጥብ 2 መድረሱን የፕሮጀክቱ የሳይት ሥራ አስኪያጅ ገለጹ።
ሥራ አስኪያጁ አቶ ፈቃዱ አብርሃም እንደገለጹት 100 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለው የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ከዴንማርክ መንግሥት በተገኘ ብድር እና ዕርዳታ ከ146 ሚሊዮን ዩሮ በላይ በጀት ግንባታው የተጀመረው ታህሳስ 8 ቀን 2013 ዓ.ም ነው።
ፕሮጀክቱ እያንዳንዳቸው 3 ነጥብ 46 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅም ያላቸው 29 የንፋስ ተርባይኖች ሲኖሩት የ22 ተርባይኖች ተከላ መጠናቀቁንና የ20ዎቹ ተርባይኖች የቅድመ ፍተሻ ሥራ መከናወኑን ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል።
እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ የኃይል ማመንጫው የባለ 230 ኪሎ ቮልት የማከፋፈያ ጣቢያ የሲቪል ሥራ ከ95 በመቶ በላይ እንዲሁም የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራ ከ60 በመቶ ደርሷል።
እያንዳንዱን ተርባይን የሚያገናኙ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች በሥራ ተቋራጩ ምክንያት መዘግየት አፈጻጸሙም 54 በመቶ ላይ እንደሚገኝና አጠቃላይ የፕሮጀክቱ አፈጻጸም 78 ነጥብ 2 መድረሱን አስታውቀዋል።
የግንባታው ሥራ ተቋራጭ ሲመንስ ጋሜሳ ሪኒዌብል ኢነርጂ የሳይት ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ኤድዋርዶ ጎንዛሌዝ እንደገለጹት ኩባንያቸው በኢትዮጵያ መሰል ፕሮጀክት ሲገነባ የመጀመሪያው ቢሆንም በሰሜን አፍሪካ ጨምሮ በበርካታ የዓለም ሀገራት የንፋስ ኃይል ማመንጫዎችን በመገንባት ልምድ እንዳለው ገልጸዋል፡፡
አሁን ላይ የፕሮጀክቱ አፈጻጸም መልካም በሚባል ደረጃ ላይ የሚገኝ መሆኑንና ቀሪ ሥራዎችን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ መሆኑንም አስረድተዋል።
የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች የአፈፃፀም ክትትልና ቁጥጥር ተወካይ ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ሰሎሞን ተረፈ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ የንፋስ ኃይል ማመንጫውን 29 የንፋስ ማማዎች ተከላ ፣ 230 ኪሎ ቮልት ማከፋፍያ ጣቢያ፣ 38 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የባለ 33 ኪሎ ቮልት የማስተላለፊያ መስመር ግንባታ ሥራዎችን ያጠቃልላል፡፡
ከእያንዳንዱ የንፋስ ማማዎች ኃይል ተቀብሎ ወደ ማከፋፈያ ጣቢያ የሚያስገባው የባለ 33 ኪሎ ቮልት የማስተላለፊያ መስመር ከሚዘረጋው 38 ኪሎ ሜትር ውስጥ የ25 ኪሎ ሜትሩ ሥራ መጠናቀቁን ተወካይ ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል፡፡
ያለቁ የንፋስ ማማዎችን በማገናኘት በአጭር ጊዜ ኃይል በማምረት ወደ ግሪድ ለማስገባት የማጠናቀቅያ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”



