በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች ላይ የሚፈፀሙ የስርቆት ወንጀሎችን ለመከላከል በተሰራው ሥራ ውጤት እየተገኘ መሆኑን በተቋሙ የኃይል መሰረተ ልማት ደህንነት፣ ክትትልና ቁጥጥር ቢሮ ገለጸ፡፡
የቢሮው ሥራ አስኪያጅ አቶ ዋለ ታምሬ እንደገለጹት በኃይል ማስተላለፊያ ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች ላይ የሚፈጸሙ የስርቆት ወንጀሎች በሀገር ደረጃ ለመከላከል በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅጣጫ ተሰጥቶበታል፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎትም ለክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች እና ለሚመለከታቸው የፀጥታ ዘርፍ ተቋማት ኃላፊዎች በኃይል መሰረተ ልማቶች ላይ እየተፈፀመ ያለው ስርቆት የሀገሪቱ ብሔራዊ የደህንነት አጀንዳ መሆኑን የማስገንዘብ ሥራ መስራቱን ተናግረዋል።
ተደጋጋሚ የስርቆት ወንጀል የሚፈፀምባቸው እና ትኩረት የሚሹ 21 መስመሮች መለየታቸውንና ተቋሙ ከብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር ጠንካራ የመረጃ ልውውጥ ስርዓት መዘርጋቱን ገልፀዋል፡፡
የሥራ ክፍሉ ባለፉት ስድስት ወራት ከተቋሙ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ጋር በመሆን በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ከሚገኙ የክልል፣ ዞንና ወረዳ አመራሮች እንዲሁም የሃይማኖት አባቶች፣ የኀገር ሽማግሌዎችና አባገዳዎች በኃይል ማስተላለፊያ መሰረተ ልማቶች ስርቆት ዙሪያ ሰባት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን ማካሄዱን ጠቅሰዋል፡፡
እንደ አቶ ዋለ ገለፃ በውይይት መድረኮቹ በተሰራው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ የቁጥጥር ሥርዓቱ ከመጠናከሩም በላይ የየአካባቢው ማህበረሰብ በመሰረተ ልማቶቹ ላይ ያለው የእኔነት ስሜት እያደገ መጥቷል፡፡
ባለፉት ስድስት ወራት በኃይል ማስተላለፊያ ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች ላይ የተፈፀመው ስርቆት ካለፉት ዓመታት ተመሳሳይ ጊዜያት ጋር ሲነፃፀር እየቀነሰ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡
በቀጣይም የታየውን መሻሻል አጠናክሮ ለማስቀጠል እና የየአካባቢው ማህበረሰብ የኃይል ማስተላለፊያ ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች በባለቤትነት ስሜት እንዲጠብቅ የሚያግዙ ስልቶች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡
የሥራ ክፍሉ አደረጃጀቱን በማጠናከር በሁሉም ቋንቋዎች የግንዛቤ ፈጠራ ሥራውን አጠናክሮ ለማስቀጠል እየሰራ ነው ያሉት አቶ ዋለ ከረጅም ጊዜ ዕቅድ አንጻር የጎረቤት ሀገራትን ልምድ ታሳቢ በማድረግ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ለመተግበር እየሰራ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”