በኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች በተከናወኑ የጥገና ሥራዎች የኃይል ምርት አፈጻጸምን ማሳደግ ተችሏል

በኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች በተከናወኑ የጥገና ሥራዎች የኃይል ምርት አፈጻጸምን ማሳደግ ተችሏል

በኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ላይ በራስ አቅም የተከናወኑ የጥገና ሥራዎች የግማሽ በጀት ዓመቱን የኃይል ምርት አፈፃፀም ማሳደጋቸውን የኃይል ማመንጫዎች ኦፕሬሽን ዘርፍ አስታወቀ።

በዘርፉ የዕቅድ ቢሮ ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ጥሩወርቅ ሽፈራው እንደገለጹት በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት በተለያዩ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ላይ በርካታ የጥገና ሥራዎች በራስ አቅም ተከናውነዋል፡፡

በተከዜ እና በጢስ አባይ 2 ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች በብልሽት ምክንያት የቆሙ ተርባይኖችን እንዲሁም በግልገል ጊቤ 2 ኃይል ማመንጫ ጣቢያ የኖዝል ጫፍ ጥገና በራስ አቅም በማከናወን የጣቢያዎቹን የኃይል ምርት ማሻሻል መቻሉን ጠቁመዋል።

እንደ ሥራ አስኪያጇ ገለፃ የኦፕሬሽንና የጥገና ሥራዎች ላይ ተጽዕኖ በማያሳድር እና የግድቦችን ደህንነት ለመጠበቅ እንዲያስችል የሞሉ ግድቦችን ውሃ የማስተንፈስ እንዲሁም የኃይል ማመንጨት ሂደቱን የሚያስተጓጉሉ የተንሳፋፊ ሳሮችን የመከላከል ተግባራት ተከናውነዋል፡፡

ለኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች የመለዋወጫ ዕቃዎችን ለማቅረብ ከቮይት ሃይድሮ፣ ኤመርሰን ኮንትሮል እና ዶንግፋንግ ኤሌክትሪክ እንዲሁም ዲራክ አውቶሜሽን ከተባሉ የውጭና የሀገር ውስጥ ኩባንያዎች ጋር የማዕቀፍ ግዥ ውል በመፈራረም ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡

ከጥገና ሥራዎቹ ጎን ለጎን የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችን የአሰራር ሥርዓት ለማዘመን የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸውንም ነው ወ/ሮ ጥሩወርቅ የተናገሩት፡፡

በጣቢያዎቹ የጥገና አስተዳደርን ለማዘመን የሚያግዙ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ጨምሮ የተሽከርካሪ አስተዳደር፣ የሥራ ፍሰትን የመቆጣጠር እና የጤናና ደህንነት አሰራሮች ተግባራዊ መደረጋቸው ጠቅሰዋል።

በጣቢያዎቹ በራስ ኃይል የተከናወኑ የጥገና ሥራዎች የኃይል ምርት አፈጻጸሙን በማሳደጋቸው ባለፉት ስድስት ወራት 13 ሺህ 504 ነጥብ 2 ጊጋ ዋት ሰዓት ኃይል እንዲመነጭ አስችሏል።

ይህም የዕቅዱን 15 ነጥብ 6 በመቶ ብልጫ ያለው መሆኑን ነው ወ/ሮ ጥሩወርቅ ያብራሩት፡፡

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top