የናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ ለሚገነባው አዲስ የኢንዱስትሪ ኮምፕሌክስ ያቀረበውን ተጨማሪ የኃይል አቅርቦት ጥያቄ ለመመለስ ከፋብሪካው ጋር ውይይት መጀመሩን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የምሥራቅ አንድ ሪጅን አስታወቀ፡፡
የሪጅኑ ዳይሬክተር አቶ ወርዲ መሀመድ እንደገለፁት ፋብሪካው ለተቋሙ ላቀረበው የኃይል አቅርቦት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ከፋብሪካው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ውይይቶች ተጀምረዋል።
በናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ የመልካ ጀብዱ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አቶ መላኩ ገብሬ በበኩላቸው ፋብሪካው በድሬዳዋ መዳረሻ መልካ ጀብዱ ላይ ሊገነባ ላሰበው የኢንዱስትሪ ኮምፕሌክስ እስከ 600 ሜጋ ዋት ተጨማሪ ኃይል ይፈልጋል ብለዋል።
የኢንዱስትሪ ኮምፕሌክሱ የሲሚንቶ ማቀነባበሪያና ማሸጊያ ከረጢቶችን ጨምሮ ለተገጣጣሚ ቤቶች፣ ለኮንክሪት እና ኖራ ማምረቻ እንዲሁም ለኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ግንባታ እና ለተለያዩ ድርጅቶች በግብዓትነት የሚያገለግሉ ምርቶችን የሚያመርቱ ፋብሪካዎችን እንደሚያካትት ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል።
እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ ፕሮጀክቱን በቅርቡ ለመጀመር የሚያስችሉ የአዋጭነት፣የአካባቢ ደህንነት፣ የመልክዓ ምድር ጥናቶች እና ሌሎች ቅድመ ዝግጅቶች ተጠናቀዋል።
የኢንዱስትሪ ኮምፕሌክሱ ለሚፈልገው እስከ 600 ሜጋ ዋት ኃይል ሪጅኑ የተለያዩ አማራጮችን እያየ መሆኑን ዳይሬክተሩ አቶ ወርዲ መሀመድ ጠቁመዋል፡፡
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

