ክልሉ በአዋሽ-ወልዲያ- ሃራ ገቢያ የባቡር የኃይል አቅርቦት ፕሮጀክት ላይ የተፈፀመውን የስርቆት ወንጀል አወገዘ

ክልሉ በአዋሽ-ወልዲያ- ሃራ ገቢያ የባቡር የኃይል አቅርቦት ፕሮጀክት ላይ የተፈፀመውን የስርቆት ወንጀል አወገዘ

የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በአዋሽ-ወልዲያ-ሃራ ገቢያ የባቡር የኃይል አቅርቦት ፕሮጀክት ላይ የተፈፀመውን የስርቆት ወንጀል በፅኑ እንደሚያወግዝ አስታውቋል።

በአስር ቀናት ውስጥ ብቻ ከ80 ኪሎ ሜትር በላይ የኮንዳክተር ሽቦ ገመድ እና 25 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር የኦ.ፒ.ጂ ደብሊው ፋይበር መስመር ለስርቆት መዳረጉን ተከትሎ የክልሉ መንግሥት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ አልተወጡም ያላቸውን የወረዳ የሥራ ኃላፊዎች ከሥልጣን ማንሳቱንም ገልጿል።

በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሃጂ አወል አርባ የተዋቀረ ኮማንድ ፖስት የስርቆት ወንጀሉ በተፈፀመባቸው የገቢረሱ ዞን ሁለት ወረዳዎች ላይ ትናንት የመስክ ምልከታ አድርጓል።

የክልሉ ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት፣ ፖሊስ ኮሚሽን፣ የሰላምና ፀጥታ ዘርፍ፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና ጠቅላይ አቃቤ ህግ ኃላፊዎችን ያካተተው ኮማንድ ፖስት ከሁሉም የዞንና ወረዳ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ተወካዮች ጋር ውይይት አድርጓል።

ውይይቱ በክልሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ የመጣውን የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ስርቆት በጋራ ለማውገዝና በወንጀሉ ዙሪያ አፋጣኝ እርምጃ ለመውሰድ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ለመምከር ያለመ ነው።

በውይይቱ ላይ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የአዋሽ-ወልዲያ-ሃራ ገቢያ የኃይል አቅርቦት ፕሮጀክት ሳይት ሥራ አስኪያጅ አቶ ተክለወይን ብርሃነአሰፋ በ2016 እና 2017 በጀት ዓመት በገቢረሱ ዞን ስር በሚገኙ ወረዳዎች ስለተፈፀሙ የኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች፣ የኮንዳክተር ሽቦ እና የኦፕቲካል ፋይበር መስመር ስርቆት መጠንና ስርቆቱ በተቋሙ ላይ ስላደረሰው ኪሳራ ለተወያዮቹ ገለፃ አድርገዋል።

በክልሉ በሁለቱ በጀት ዓመት ብቻ በኃይል መሰረተ ልማቶች ላይ በተፈፀመ ስርቆት ሳቢያ ከ717 ሺህ ዶላር በላይ እና ከ25 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ መድረሱን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሰሜን ምስራቅ ሁለት ሪጅን የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ሀሰን መሐመድ እንደገለፁት ሪጅኑ ሦስት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎችን እና ከ436 ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍኑ የማስተላለፊያ መስመሮችን ያስተዳድራል።

ተቋሙ ለህብረተሰቡ ኤሌክትሪክ ለማዳረስ በሚያደርገው ጥረት ውስጥ በኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎችና የኮንዳክተር ሽቦ ላይ የሚፈፀመው የስርቆት ወንጀል ማነቆ እንደሆነ አስረድተዋል።

በውይይቱ ላይ የዞንና የወረዳ እንዲሁም  የፀጥታ ዘርፍ አካላት በኃላፊነት ስሜት መንቀሳቀስ አለመቻላቸው በኃይል መሰረተ ልማቶቹ ላይ ከፍተኛ የዝርፊያ ወንጀል እንዲፈፀም በር ከፍቷል ተብሏል።

የስርቆት ወንጀሉን ከምንጩ ለማድረቅ በየደረጃው ያሉ ሁሉም የክልሉ አመራሮች በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባም ነው ኮማንድ ፖስቱ አቅጣጫ ያስቀመጠው።

ኮማንድ ፖስቱ በክልሉ የሚገኙ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን ደህንነት ለመጠበቅ ያስችላል ያለውን የመግባቢያ ሥምምነት ከሁሉም የዞንና የወረዳ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተፈራርሟል።

ሥምምነቱ በኃይል መሰረተ ልማት ስርቆት ላይ የሚሳተፉ ወንጀለኞችን ተከታትሎ ለፍርድ ለማቅረብና በየደረጃው በሚገኙ አመራሮች ላይ ተጠያቂነትን ለማስፈን እንዲያስችል እንዲሁም ወንጀሉ ዳግም እንዳይከሰት ለማድረግ ያስችላል ተብሏል።

ህብረተሰቡ መሰረተ ልማቶቹን በእኔነት ስሜት እንዲጠብቅ ለማድረግ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እስከታችኛው የክልሉ የአስተዳደር መዋቅር ድረስ በአስቸኳይ እንዲሰራም ውሳኔ ላይ ተደርሷል።

በውይይቱ ላይ የአፋር ክልል ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጎልቤ ሲሌን ጨምሮ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ሙሳ አብዶ፣ የክልሉ የሰላምና ፀጥታ ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ ሁሴን መሐመድ፣ የክልሉ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢስማኤል መሐመድ እና የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ቢልኤ አህመድ እንዲሁም የዞንና የወረዳ የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top