የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ የባለ 230 ኪሎ ቮልት የማከፋፈያ ጣቢያ የፍተሻና የሙከራ ሥራ ለማከናወን የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተሰራ መሆኑን የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ተናገሩ፡፡
ሥራ አስኪያጁ አቶ ጌቱ ያደታ እንደተናገሩት የተጠናቀቁ የንፋስ ማማዎችን ከቆቃ- መልካዋከና ከሚያልፈው የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ጋር በማገናኘት ኤሌክትሪክ ወደ ብሔራዊ የኃይል ቋት ለማስገባት ጥረት እየተደረገ ነው፡፡
ፕሮጀክቱ በተለያዩ ምክንያቶች በዕቅዱ ከተቀመጠው ጊዜ በላይ ቢወስድም በአሁኑ ወቅት በንዑስ ሥራ ተቋራጮቹ አማካኝነት የ20ዎቹ ተርባይኖች የቅድመ ፍተሻ ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል።
እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ በኃይል ማከፋፈያ ጣቢያው ላይ የሙከራና የፍተሻ ሥራው ከተጠናቀቀ በኋላ የቅድመ ፍተሻ የተከናወነላቸውን ተርባይኖች በሂደት ወደ ግሪድ የማስገባት ሥራ ይሰራል።
በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ በየሳምንቱ 10 ሜጋ ዋት በድምሩ 80 ሜጋ ዋት ወደ ብሔራዊ የኃይል ቋት ለማስገባት ታቅዶ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በፕሮጀክቱ የተቋሙ የራስ ኃይል መምሪያ ተወካይ አስተባባሪ አቶ ቴዎድሮስ ጋሻው በበኩላቸው የራስ ኃይል መምሪያ በፕሮጀክቱ የሁለት የኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎችና የሽቦ ዝርጋታ ሥራን በ3 ክሬኖች እያከናወነ ነው ብለዋል።
ሥራውን በሁለት ቀናት ውስጥ በማጠናቀቅ ከቆቃ-መልካዋከና ከተዘረጋው ባለ 230 ኪሎ ቮልት የማስተላለፊያ መስመር ላይ በመቀጠል የማከፋፈያ ጣቢያውን ለሙከራና የፍተሻ ሥራ ዝግጁ ለማድረግ እየተሰራ ነው።
በተመሳሳይ የበቆጂ ባለ230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ የፍተሻና የሙከራ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።
የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ እንደ አገር ከንፋስ የሚመነጨውን ኃይል ከ404 ሜጋ ዋት ወደ 504 ሜጋ ዋት ከፍ በማድረግ የኃይል ስብጥሩን ለማሳደግና አስተማማኝ ኃይል ለማቅረብ ያስችላል፡፡
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”




