ለሠራተኞች የሥራ ላይ ደህንነት ቅድሚያ ተሰጥቶ እየተሠራ ነው

ለሠራተኞች የሥራ ላይ ደህንነት ቅድሚያ ተሰጥቶ እየተሠራ ነው

በግንባታ ሥራ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ ሠራተኞችን ጤንነትና ደህንነት ለመጠበቅ ለሥራ ላይ ደህንነት ቅድሚያ ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የደቡባዊ የኤሌክትሪክ ግሪድ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ሳይት ሁለት አስታወቀ፡፡

የፕሮጀክቱ ሥራ ተቋራጭ ሃይሰን ሄቪ ኢንደስትሪ ኮርፖሬሽን የሳይት ሁለት የሥራ ቦታ ደህንነትና የሠራተኛ ጤንነት ቁጥጥር ሥራ አስኪያጅ አቶ ባህሩ በቀለ እንዳስታወቁት የቲርጋና ሽግዳን ማከፋፈያ ጣቢያዎች እና የማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክት ከከተማ ርቆ የሚገኝ በመሆኑ የሚያጋጥሙ አደጋዎችን ቀድሞ ለመከላከል እና የሠራተኞችን ጤንነት ለማረጋገጥ በሳይቱ የሥራ ላይ ደህንነት የሥራ ክፍል በማቋቋም ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡

በግንባታ ሥራ ላይ የሚሳተፉ ሠራተኞች ለተለያዩ አደጋዎች ተጋላጭ በመሆናቸው በሥራ ላይ የሚደርሱ የተለያዩ አደጋዎችን ለመከላከል የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

ሠራተኛው ሥራ ከመጀመሩ በፊት ስለ አደጋ አጋላጭ ሁኔታዎች፣ ስለአደጋ መከላከያ መንገዶች፣ ሠራተኞች በስራ ቦታቸው ላይ ስለሚኖራቸው እንቅስቃሴ እንዲሁም ከደህንነት መሳሪያዎች አጠቃቀም ጋር በተያያዘ የግንዛቤ ማስጨበጫ በየጊዜው እንደሚሰጥ አመልክተዋል፡፡

በሥራው ላይ አደጋ ቢያጋጥም ለተጎጂዎቹ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት በሥራ ቦታዎች ላይ የመጀመሪያ እርዳታ መስጫ ክፍል  መዘጋጀቱንና ከአቅም በላይ ከሆነ ደግሞ ወደ ህክምና ተቋማት የሚላኩበት አሰራር መዘርጋቱን ሥራ አስኪያጁ አንስተዋል፡፡

የሥራ ላይ ደህንነት መጠበቂያ መንገዶችን በማያከብር ሠራተኛ ላይ እስከ ሥራ ማሰናበት የሚደርስ አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወሰድም አስታውቀዋል፡፡

እንደ አቶ ባህሩ ገለፃ ሠራተኛው የሥራ ላይ ደህንነት ጉዳይን ባህል በማድረጉ እና አስፈላጊው ክትትልና ቁጥጥር በመደረጉ እስከ አሁን ምንም አይነት አደጋ አላጋጠመም፡

በሽግዳን ማከፋፈያ ጣቢያ የግንባታ ሥራ ላይ በአናፂነትና በረዳት ፎርማን እየሰሩ የሚገኙት  ጃኪ አይቾሚ እና አሳየኸኝ አሻግሬ በበኩላቸው በፕሮጀክቱ የሥራ ቦታ ለአደጋ እንዳይጋለጡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ከመስጠት ጀምሮ የአደጋ መከላከያ መሳሪያዎች እንደሚቀርብላቸው ተናግረዋል፡፡ 

የሚሰጣቸውን የግንዛቤ ማስጨበጫ እና የአደጋ መከላከያ መሳሪያዎችን በአግባቡ በመተግበር ደህንነታቸውን ጠብቀው እየሠሩ እንደሆነም አረጋግጠዋል፡፡

በደቡባዊ የኤሌክትሪክ ግሪድ ማስፋፊያ ፕሮጀክት በሳይት ሁለት በሚከናወኑ የግንባታ ሥራዎች ላይ ከአንድ ሺ በላይ ሠራተኞች እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top