በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ባለፉት አምስት ዓመታት በማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ በተከናወኑ የአቅም ማሳደግና የማዘመን ሥራዎች ተጨማሪ 310 ሜጋ ዋት ኃይል ማግኘት መቻሉን በተቋሙ የሪጅኖች ማስተባበሪያ መምሪያ አስታወቀ፡፡
የመምሪያው ዳይሬክተር አቶ ጋሻው እንድሪያስ እንዳስታወቁት ከከተሞችና ከኢንዱስትሪ መስፋፋት ጋር ተያይዞ በየጊዜው እያደገ የመጣውን የኃይል ፍላጎት ለማሟላት ከአዳዲስ የኃይል መሰረተ ልማት ግንባታዎች በተጨማሪ በነባር ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ የአቅም ማሳደግ፣ የማስፋፊያ እና ማዘመን ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡

የማከፋፈያ ጣቢያዎች ዕድሜ፣ የኃይል ጭነት ከመጠን በላይ መሆን እና በጣቢያዎች ላይ በሚከሰቱ ድንገተኛ ችግሮች በዕቃዎች ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች ለአቅም ማሳደግ እና ማሻሻያ ሥራዎች መከናወን ምክንያት እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡
ሥራው በስዊች ጊሮች፣ ትራንስርመሮች፣ ቮልቴጁን በሚያመጣጥኑ ሸንት ሪያክተሮች እና በሌሎች ዋና ዋና የማከፋፈያ ጣቢያ አካላት ላይ እንደሚከናወንም ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል፡፡
እንደ አቶ ጋሻው ገለፃ ባለፉት አምስት ዓመታት በነባር ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ 22 የሚሆኑ ፓወር ትራንስፎርመሮችን በመትከል 310 ሜጋ ዋት ተጨማሪ ኃይል ማግኘት ተችሏል፡፡
የጣቢያዎቹን የመቆጣጠሪያ ብሬከሮች (switchgear) አቅም የማሳደግና የማዘመን ሥራዎች በመሰራታቸው ትራንስፎርመሮቹ በተሻለ አቅም እንዲሰሩ ማድረግ መቻሉን አስታውቀዋል፡፡
በ75 ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ ለማከናወን ከታቀደው የመቆጣጠሪያ ብሬከር ቅየራ ሥራዎች እስከ አሁን የ25ቱ መጠናቀቁን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ በተያዘው ዓመት የአስር ጣቢያዎችን ለማጠናቀቅ ታቅዶ እየተሰራ ነውም ብለዋል፡፡
ቦሌ ለሚ፣ ሻሸመኔ፣ ጂግጂጋ፣ በደሌ፣ ሐረር II እና III፣ ወልቂጤ፣ ደብረ ታቦር፣ ጊንጭ፣ ደብረ ብርሃን፣ ድሬዳዋ II እና III፣ አሸጎዳ፣ ገላን፣ ሆሳዕና፣ ባህርዳር II፣ ጌዶ እና ጋሸና ማከፋፈያ ጣቢያዎች የአቅም ማሳደግ፣ ማስፋፊያ እና የማዘመን ሥራዎች ከተከናወኑባቸው መካከል ተጠቃሾች ናቸው፡፡
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”





የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ይፋዊ የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን በመቀላቀል ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ያግኙ
ፌስቡክ↠ https://www.facebook.com/Ethioelectric
ቴሌግራም↠ https://t.me/EEPCommuication
ትዊተር ↠ https://twitter.com/EEPethiopia
ዩትዩብ ቻናል↠ https://www.youtube.com/@ethiopowermedia
ቲክቶክ አካውንት↠https://tiktok.com/@ethio_power
ድረ – ገፃችንንም ይጎብኙ www.eep.com.et
መጋቢት 2 ቀን 2017 ዓ.ም