ከደቡባዊ የኤሌክትሪክ ግሪድ ማስፋፊያ ፕሮጀክት የዕውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር እየተገኘበት መሆኑን በፕሮጀክቱ የሳይት ሁለት ሥራ አስኪያጅ አስታወቁ፡፡
ሥራ አስኪያጁ አቶ አርጋዉ ታዲ እንዳስታወቁት በደቡባዊ የኤሌክትሪክ ግሪድ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ሳይት ሁለት በሚከናወኑ የማከፋፈያ ጣቢያና ማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክት ላይ 80 የውጭ ሀገር ዜጎች እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡
ከግንባታ ሥራዎቹ የዕውቀት እና ቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር ለማድረግ በሥራው ላይ እየተሳተፉ ያሉ ኢትዮጵያዊያንን ከውጭ ሀገር ዜጎች ጋር በማቀናጀት እንዲሰሩ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
ይህም ወደፊት የሚከናወኑ ሥራዎችን በራስ ኃይል ለማከናወን የሚያስችል አቅም ለመፍጠርና የሥራ ባህልን ለማሳደግ እንደሚያግዝ ነው አቶ አርጋው ያስታወቁት፡፡
በባዮክሰን ኢንጂነሪንግ አማካሪ ሲቪል መሃንዲስ አቶ አብርሃም ደሳለኝ በበኩላቸው የውጭ ሀገራት ዜጎች በፕሮጀክቱ የግንባታ ሥራዎች መሳተፋቸው ብቁ ሠራተኞችን ለማፍራት ያግዛል ብለዋል፡፡
በሽግዳን ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ የሲቪል መሐንዲስ የሆኑት አቶ መኮንን ጥላሁን በበኩላቸው እንደተናገሩት ከውጭ ሀገር ዜጎች ጋር መስራቱ ክህሎትን ለማዳበር፣ ቴክኖሎጂና ልምድ ለመቅሰም ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል፡፡
በሽግዳን ማከፋፈያ ጣቢያ በረዳት ፎርማንነት እየሰራ የሚገኘው አሳየኸኝ አሻግሬ እንደገለፀው ወደ ፕሮጀክቱ ከመቀላቀሉ በፊት ከሹፍርና ውጭ ከግንባታ ሥራዎች ጋር በተያያዘ ምንም አይነት ዕውቀትና ልምድ አልነበረውም፡፡
ይሁንና ፕሮጀክቱን በተቀላቀለ በአንድ አመት ከስድስት ወር ውስጥ የተለያዩ ሙያዎች ባለቤት እንደሆነና ለዚህ ደግሞ ከውጭ ዜጎች ጋር አብሮ መስራቱ ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚወስድ ተናግሯል፡፡
በሳይት ሁለት በሚከናወኑ የሽግዳንና ቲርጋ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች እንዲሁም ከሳውላ ቲርጋ በሚዘረጋው የማስተላለፊያ መስመር ላይ ከአንድ ሺህ በላይ ሠራተኞች እየተሳተፉ መሆናቸውን ከዚህ በፊት መዘገባችን ይታወሳል፡፡
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”





