በከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ላይ በተፈፀመ ስርቆት አራት ታወሮች ወድቀዋል

በከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ላይ በተፈፀመ ስርቆት አራት ታወሮች ወድቀዋል

ከባህርዳር – ወልዲያ – ኮምቦልቻ በተዘረጋው ባለ 400 ኪሎ ቮልት የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ላይ በተፈፀመ ስርቆት አራት የኃይል ተሸካሚ ምሶሶዎች መውደቃቸውን ፕሮጀክቱ አስታወቀ፡፡

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የባህርዳር – ወልዲያ – ኮምቦልቻ ፕሮጀክ የሳይት ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮሐንስ ኪሮስ እንዳስታወቁት ስርቆቱ የተፈፀመው መጋቢት 2 ቀን 2017 ዓ.ም በደቡብ ጎንደር ደብረታቦር ከተማ አቅራቢያ ጉና ወረዳ ነው።

በተፈፀመው ስርቆት አራት የከፍተኛ ኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎች በሙሉ መውደቃቸውን ያረጋገጡት ሥራ አስኪያጁ በስርቆቱ 129 ሚሊዮን ብር የሚገመት ኪሳራ በተቋሙ ላይ ደርሷል ብለዋል።

በስርቆትና በፀጥታ መደፍረስ ሲፈተን የቆየውን ፕሮጀክት በማጠናቀቅ ከግሪድ ጋር ለማገናኘት ተቋሙ ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ በሚገኝበት ወቅት ችግሩ መፈጠሩ እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ የፕሮጀክቱ አፈጻጸም 87 በመቶ ቢደርስም በፕሮጀክቱ ላይ የሚፈፀሙ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የብረት ምሰሶ ስርቆቶች ለሥራው እንቅፋት መሆናቸውን ሥራ አስኪያጁ አመልክተዋል።

ስለሆነም ቀሪ የፕሮጀክቱን ሥራዎች በአጭር ጊዜ አጠናቆ አገልግሎት ለማስጀመር ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለችግሩ ልዩ ትኩረት ሊሰጡት እንደሚገባ አሳስበዋል።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top