ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ የከተማዋን የኃይል አቅርቦት አቅም በአራት እጥፍ ያሳድጋል

ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ የከተማዋን የኃይል አቅርቦት አቅም በአራት እጥፍ ያሳድጋል

የደሴ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ የከተማዋን የኃይል አቅርቦት አቅም በአራት እጥፍ እንደሚያሳድግ የትራንስሚሽን ቢዝነስ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አስታወቁ።

በምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚው ኢንጂነር አንዱዓለም ሲዓ የተመራ የልዑካን ቡድን በመገንባት ላይ ያለውን የደሴ ባለ 230 ኪሎ ቮልት ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት በመስክ በመገኘት ገምግሟል።

ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚው በጉብኝቱ ወቅት እንደገለፁት ከተሞቻችን የሚያስፈልጋቸውን የኤሌክትሪክ ኃይል ለማሟላት ተቋሙ ከመቼውም ጊዜ በላይ በቁርጠኝነት እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡

የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር የደሴ ከተማን የኤሌክትሪክ ፍላጎት አቅም ለሚቀጥሉት 20 ዓመታት መሸከም የሚችል ነው ብለዋል፡፡

ፕሮጀክቱን በተያዘው በጀት ዓመት መጨረሻ አጠናቆ ወደ ሥራ ለማስገባት ዕቅድ መያዙን የጠቀሱት ኢንጂነር አንዱዓለም የኃይል ማስተላለፊያ መስመሩን ለመገንባት ከተማ አስተዳደሩ ለካሳና ተያያዥ ጉዳዮች አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

እንደ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገለፃ ለፕሮጀክቱ ግንባታ የሚያስፈልጉ ተጨማሪ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ዕቃዎችን በቅርቡ ወደ ሳይት የማጓጓዝ ሥራዎች ይጀመራሉ፡፡

ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ብቻ አይደለም ያሉት ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚው ከተማ አስተዳደሩ የግንባታውን ሂደት በቅርበት እየተከታተለ እገዛ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የደሴ ከተማ አስተዳደር ተወካይ ከንቲባ ኮማንደር ሰዒድ ዓሊ እንደገለፁት በከተማዋ የሚስተዋለውን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እና ፍላጎት ያለመጣጣም ችግር  ለመቅረፍ ከተማ አስተዳደሩ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር በቅርበት ይሰራል፡፡

ከፕሮጀክቱ ጋር ተያይዘው ለሚነሱ ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ከተማ አስተዳደሩ ከመቼውም ጊዜ በላይ ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top