
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በደሴ ከተማ አስተዳደር ስር ለሚገኘው የጢጣ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተለያዩ የትምህርት ግብዐቶችን ድጋፍ አደረገ።
ድጋፉን የተቋሙ የትራንስሚሽን ቢዝነስ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አንዱዓለም ሲዓ ለከተማ አስተዳደሩ ተወካይ ከንቲባ ኮማንደር ሰዒድ አሊ አስረክበዋል።
የደሴ ከተማ አስተዳደር ተወካይ ከንቲባ ኮማንደር ሰዒድ ዓሊ በርክክብ ሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደተናገሩት ድጋፉ በትምህርት ቁሳቁስ እጥረት ምክንያት ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ እገዛ ያደርጋል።
የተደረገው ድጋፍ ወቅቱን የጠበቀ በመሆኑ የትምህርት ግብዓቶችን መግዛት ለማይችሉ ወላጆች ትልቅ እፎይታን የሰጠ ነው ብለዋል።
የጢጣ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከደሴ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ፕሮጀክት አቅራቢያ እንደሚገኝ የጠቀሱት ተወካይ ከንቲባው ይህም ህብረተሰቡ በፕሮጀክቱ ላይ የእኔነት ስሜት እንዲሰማው እንደሚያደርግ አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለትምህርት ዕድገት እያበረከተ ያለውን አስተዋፅኦ አድንቀው በቀጣይ መሰል ድጋፎችን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
በተቋሙ የዋና ሥራ አስፈፃሚ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሙላት ገዛኸኝ እንደተናገሩት ትምህርት አምራች ትውልድን ለመፍጠር ትልቅ መሳሪያ መሆኑን ስለሚረዳ ከትምህርት ገበታቸው የራቁ ተማሪዎችን ለመመለስ እየተደረገ ያለውን ጥረት ተቋሙ ይደግፋል።
ድጋፉ 250 ለሚደርሱ የጢጣ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የጽህፈት መሳሪያዎች እና የደብተር መያዣ ቦርሳዎችን ያካተተ ሲሆን ለዚህም ተቋሙ 825 ሺህ ብር ወጪ ማደረጉን ተናግረዋል።
ተቋሙ የትምህርት ጥራትን ለማረጋጋጥ በትውልድ ልማት ሥራዎች ላይ አሻራውን እያሳረፈ እንደሚገኝ ጠቅሰው በቀጣይም መሰል ድጋፎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።
በርክክብ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የከተማ አስተዳደሩ የትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊዎች እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ተወካዮች ተገኝተዋል።
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”



