ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ለከተማዋ የኃይል አቅርቦት ቁልፍ ድርሻ ያበረክታል

ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ለከተማዋ የኃይል አቅርቦት ቁልፍ ድርሻ ያበረክታል

በባህር ዳር ከተማ እየተገነባ የሚገኘው ባለ 230 ኪሎ ቮልት ተንቀሳቃሽ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ሲጠናቀቅ በከተማዋ እና በአካባቢው አስተማማኝ ኃይል ለማቅረብ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሰሜን ምዕራብ ሪጅን መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ተሻገር እንደገለፁት በከተማዋ አንድ ባለ 400/230 ኪሎ ቮልት የማከፋፈያ ጣቢያ የሚገኝ ቢሆንም ጣቢያው የነዋሪውን የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት ጥያቄ በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል አልነበረም፡፡

ነባሩ ማከፋፈያ ጣቢያ ለባህር ዳር ከተማና ለአካባቢው ኢንዱስትሪዎች 125 ሜጋ ዋት ኃይል እያቀረበ መሆኑን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ ሆኖም ጣቢያው ኃይል የመጫን አቅሙ በመሙላቱ ምክንያት ተጨማሪ ጥያቄዎችን ማስተናገድ የማይችልበት ደረጃ ላይ መድረሱን ገልፀዋል።

አዲስ በመገንባት ላይ የሚገኘው ተንቀሳቃሽ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ተጨማሪ 48 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ በማቅረብ በከተማዋ የሚስተዋለውን የኃይል መቆራረጥ እና የቮልቴጅ መዋዠቅ ችግር ይፈታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ነው ያብራሩት፡፡

ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ ተጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ እንዲሆን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እና የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር የተለያዩ ግብዓቶችን በማቅረብ በኩል ከፍተኛ እገዛ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ መላኩ ተስፋዬ በበኩላቸው ጣቢያው 50 ሜጋ ቮልት አምፒር ኃይል የመጫን አቅም ያለው አንድ ትራንስፎርመር እንዲሁም አንድ ባለ 230 ኪሎ ቮልት ገቢ እና ስድስት ባለ 15 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮች እንዳሉት ገልፀዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ለወጪ መስመሮች የሚያገለግሉ የኮንክሪት ምሰሶዎች ተከላ መጠናቀቁን ጠቅሰው የኬብል ቀበራ እና የአጥር ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለጣቢያው አገልግሎት የሚውለውን ትራንስፎርመር ለማጓጓዝ የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም አብራርተዋል።

እንደ አቶ መላኩ ገለፃ የፕሮጀክቱ ግንባታ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ ከባህር ዳር ከተማ በተጨማሪ የሐሙሲት ከተማ እና በዙሪያው የሚገኙ አካባቢዎች የኃይል አቅርቦቱ ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡

ፕሮጀክቱን በተያዘው ወር መጨረሻ ላይ በማጠናቀቅ አገልግሎት ለማስጀመር ርብርብ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top