ፕሮጀክቱ ለአካባቢው ወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጥሯል

ፕሮጀክቱ ለአካባቢው ወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጥሯል

የገዳ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት ለአካባቢው ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠሩን የሳይት ሥራ አስኪያጁ ተናገሩ።

ሥራ አስኪያጁ አቶ ቴዎድሮስ ጋሻው እንደተናገሩት ፕሮጀክቱ 190 ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ፈጥሯል።

የአካባቢው ወጣቶች በፕሮጀክቱ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙ የተናገሩት አቶ ቴዎድሮስ ይህም ወጣቶቹ በተፈጠረላቸው የሥራ ዕድል ተጠቅመው ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን እንዲያስተዳድሩ ዕድል መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡

በሜካኒካል ኢንጅነሪንግ ተመርቆ ሥራ አጥ ሆኖ መቆየቱን የጠቀሰው ወጣት ጌታቸው ገብሬ አሁን ላይ በፕሮጀክቱ የዕቃ ግምጃ ቤት ሠራተኛ ሆኖ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግሯል።

በፕሮጀክቱ በተፈጠረለት የሥራ ዕድል ከሥራ አጥነት ወጥቶ ራሱንና ቤተሰቡን እያስተዳደረ መሆኑንም ጠቁሟል።

ከዕቃ ግምጃ ቤት ሥራው ጎን ለጎን ከሰለጠነበት ሙያ ጋር ተያያዥ በሆኑ ስራዎች ላይ እንዲሳተፍ ዕድል እንደፈጠረለት የተናገረው ወጣት ጌታቸው በቀጣይ በሙያው ተቀጥሮ በመሰል ፕሮጀክቶች ላይ በመሳተፍ ሀገሩን እንደሚያገለግል እምነት እንዳለው ገልጿል።

ሌላኛዋ የሥራ ዕድሉ ተጠቃሚ ወጣት ትህትና ብርሃኑ በበኩሏ በፕሮጀክቱ የሥራ ሰዓት ተቆጣጣሪ በመሆን እየሰራች መሆኑን ገልጻለች።

የማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክቱ በአካባቢው መጀመር በፈጠረላት የሥራ ዕድል የተሻለ ገቢ ለማግኘት እንደረዳት እና ሌሎች የአካባቢው ወጣቶችም የዚሁ ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግራለች፡፡

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top