በቅየሳ ሥራ ለረጅም ዓመታት ላገለገሉ ሴት ሠራተኞች ዕውቅና ተሠጠ

በቅየሳ ሥራ ለረጅም ዓመታት ላገለገሉ ሴት ሠራተኞች ዕውቅና ተሠጠ

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኢንጂነሪንግ ዘርፍ ለ36 ዓመታት በቅየሳ ሥራ ላይ ላገለገሉ ሦስት ሴት ሠራተኞች በዛሬው ዕለት ዕውቅና ሰጥቷል።

የዘርፉ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ውድነህ የማነ በዕውቅና መርሀግብሩ ላይ እንደተናገሩት የቅየሳ ሥራ ተቋሙ ለሚያከናውናቸው የመሠረተ ልማት ግንባታ ሥራዎች ቀዳሚውን ድርሻ ይይዛል።

ሠራተኞቹ አሁን የደረስንበት ቴክኖሎጂ ላይ ሳንደርስና ሴትነታቸው ሳይበግራቸው ለተቋሙ ላበረከቱት አስቸዋጽዖ አመስግነው በቀጣይ ጊዜ  ልምዳቸውን ለሌሎች በማካፈል ለተቋሙ የሚያደርጉትን አስተዋፅዖ አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።

ሠራተኞቹ ለረጅም ዓመታት በአንድ መደብ መስራታቸው ከራሳቸው ይልቅ ለተቋሙ ቅድሚያ መስጠታቸውን የሚያሳይ በመሆኑ ሌሎች ሠራተኞችም ይህን አርዓያ ተከትለው ለተቋሙ ስኬት የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል።

በዘርፉ የቴክኒካል ድጋፍ መምሪያ ዳይሬክተር አቶ አብዱልአሊም አህመድ በበኩላቸው ዕውቅናው ሠራተኞቹ ለሥራ አመቺ ያልሆኑ አስቸጋሪ የሥራ ሁኔታዎችን ተቋቁመው ያገለገሉበትን ዘመን ታሳቢ ያደረገ ነው።

በዛሬው ዕለት የተሰጠው ዕውቅና ሌሎች ሠራተኞች የፈጠራ ችሎታቸውን አዳብረው ለተቋሙ ስኬት በርትተው እንዲሰሩ ተነሳሽነትን እንደሚፈጥርም ተናግረዋል።

በቀጣይ ዘርፉን ለማሳደግ ጥረት ለሚያደርጉ ሠራተኞች የሚሠጠው  እውቅና ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ በመገኘት መልዕክት ያስተላለፉት በተቋሙ የሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ዳይሬክተር ወ/ሮ ሌንሴ ኢደኤ ዕውቅና የተሠጣቸው ሠራተኞች ሴቶች በማንኛውም ዘርፍ እንደሚችሉና ውጤታማ እንደሚሆኑ በተግባር አሳይተውናል በማለት ገልፀዋል።

ዘርፉ ለሴት ሠራተኞች ለሠጠው ዕውቅና አመስግነው ሌሎች የሥራ ክፍሎች ይህን አርዓያ እንዲከተሉ እና ለሴቶች ምቹ የሥራ ከባቢ ለመፍጠር የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳሰበዋል።

በዕለቱ ዕውቅና ከተሰጣቸው ሠራተኞች መካከል ተቋሙን ከ1981 ዓ.ም ጀምር በቅየሳ ሥራ ያገለገሉት ወ/ሮ አባይነሽ ፅጌ እንደተናገሩት በአንድ መደብ ላይ ለረጅም ዓመታት ማገልገል የራስን ልምድ ከማዳበሩም ባለፈ ለተቋሙ ውጤታማነት ከፍተኛ ፉይዳ ይኖረዋል።

የቅየሳ ሥራ ተቋሙ ለሚያከናውናቸው ሥራዎች “የጀርባ አጥንት” ነው የሚሉት ወ/ሮ አባይነሽ ተቋሙም ሥራው ለዘርፉ የሚኖረውን ፋይዳ በመገንዘብ ለሠጣቸው እውቅና አመስግነው ዕውቅናው በቀሪ ጊዜያቸው ለሚያከናውኑት ሥራ  ስንቅ እንደሚሆናቸው ተናግረዋል።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top