በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የመልካ ዋከና ኃይል ማመንጫ ጣቢያ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በተሻሉ መምህራን ጥራት ያለው ትምህርት በመስጠቱ በአካባቢው ማህበረሰብ ተመራጭ እየሆነ መምጣቱን የት/ቤቱ ምክትል ርዕሰ መምህር ገለፁ።
ምክትል ርዕሰ መምህሩ ጫላ ደሜ እንደገለፁት ትምህርት ቤቱ የጣቢያው ሠራተኛ ልጆች እንዲማሩ ታስቦ ቢከፈትም በሂደት የአካባቢውን ማህበረሰብ ልጆችን ተጠቃሚ ማድረግ ጀምሯል፡፡
የኃይል ማመንጫ ጣቢያው ለትምህርት ቤቱ የግብዓት ድጋፍ የሚያደርግ ከመሆኑ ባሻገር ለመምህራን የመኖሪያ ቤት፣ የትራንስፖርት፣ መብራትና ውሃ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል።
የጣቢያው የአስተዳደር፣ ንብረትና ጠቅላላ አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ ተሻገር በበኩላቸው እንደተናገሩት ጣቢያው ኃይል ከማመንጨት ባሻገር ትውልድ ቀረጻ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።
ትምህርት ቤቱ የሚተዳደረው በክልሉ ትምህርት ቢሮ በኩል ቢሆንም ጣቢያው ክትትልና የተለያዩ ድጋፎችን እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
በትምህርት ቤቱ የ8ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ሙዘሚር ሙሐመድ እንዲሁም የ6ኛ ክፍል ተማሪ የሆኑት ተማሪ ፈትያ ጀማል እና ተማሪ ሮቤ አለሙ ቱሉ እንደገለጹት የትምህርት ቤቱ መከፈት ከቤተሰብ ሳይርቁ የመማር እድል ፈጥሮላቸዋል።
ጣቢያው የከፈተው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ለአካባቢው ልጆች የመማር ተስፋ መፈንጠቁን ገልጸዋል።
ጣቢያው ትምህርት ቤቱን ከመክፈት በተጨማሪ ተማሪዎች ሲታመሙ በጣቢያው ክሊኒክ የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ትምህርት ቤቱ በአሁኑ ወቅት ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል 876 ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ መሆኑን ተናግረዋል።
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”


