በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የይርጋለም ቁጥር አንድ እና ሁለት የኃይል ማከፋፊያ ጣቢያዎችን ጎብኝቷል።
ቋሚ ኮሚቴው ያደረገው ጉብኝት በጣቢያው የታዩ የኦዲት ግኝቶችን መሠረት ያደረገ የእርምት እርምጃ ስለመውስዱ እንዲሁም በኦዲት ግኝቱ ወቅት የተቀመጡ አቅጣጫዎች ተግባራዊ ስለመደረጋቸው በመስክ ተገኝቶ ለመገምገም ያለመ ነው።
የቋሚ ኮሚቴው አባላት ስለማከፋፈያ ጣቢያዎቹ አሰራር እና ተቋሙ የኃይል ፍሰቱን የሚቆጣጠርበትን ሥርዓት በተመለከተ በጣቢያው ኃላፊዎች ገለፃ የተደረገላቸው ሲሆን ጣቢያዎቹን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ እና የቡድኑ አስተባባሪ የተከበሩ ወ/ሮ አራሬ ሞሲሳ ከኦዲት ግኝቱ ጋር ተያይዞ የንብረት አያያዝ፣ የካሳ ክፍያ እና ለአካባቢው ማህበረሰብ የተሰጠ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስለመኖሩ እና የማስተካከያ እርምጃዎች ስለመወሰዳቸው በመስክ ምልከታው ወቅት አንስተዋል።
ተቋሙ በፕሮጀክቶች ላይ የሚታየውን የፋይናንስና የግብዓት እጥረት በመቅረፍ የሀገር ሀብትን ከብክነት ለመጠበቅ በግኝቶቹ ላይ ማስተካከያና የእርምት እርምጃ መውሰድ እና ሊያሰሩ የሚያስችሉ የአሰራር ስርዓቶችን መዘርጋት እንደሚያስፈልገው ምክትል ሰብሳቢዋ አሳስበዋል።
ተቋሙ የፕሮጀክቶች ግንባታ ሥራን በሚመለከት ለህብረተሰቡ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ በመስራት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር የጀመረውን ቅንጅታዊ አሠራርን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባው አመልክተዋል።
ቋሚ ኮሚቴው የሀዋሳ ቁጥር አንድ እና ሁለት ማከፋፈያ ጣቢያዎችንም ጎብኝቷል።
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”



