በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የአይሻ 3 የንፋስ ኃይል ማመንጫ ግንባታን ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን የተቋሙ የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ገለጹ፡፡
ዳይሬክተሩ አቶ ሞገስ መኮንን እንደገለጹት የአይሻ የንፋስ ኃይል ማመንጫ 120 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም እንዲኖረው ታስቦ እየተገነባ ያለ ፕሮጀክት ሲሆን በአሁኑ ጊዜ አፈጻጸሙ 83 ነጥብ 8 በመቶ ደርሷል፡፡
ግንባታው ደረጃ በደረጃ እየተሠራ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሞገስ ፕሮጀክቱ 80 ሜጋ ዋት ኃይል ወደ ብሔራዊ የኃይል ቋት እያስገባ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ቀሪውን 40 ሜጋ ዋት ኃይል የሚያመነጩ ተርባይኖችን የመትከል ሥራ ለማከናወን የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ተርባይኖችን የመትከል ሥራው በፋይናንስ አቅርቦት ምክንያት መዘግየቱን ያስታወሱት ዳይሬክተሩ አሁን ላይ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አበዳሪዎችን ሳይጠብቅ በራሱ ፋይናንስ ግንባታውን ለማጠናቀቅ ወስኖ ወደ ሥራ መግባቱን አብራርተዋል፡፡
በኢትዮጵያ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ታሪክ የአዳማ አንድ እና ሁለት እንዲሁም የአሸጎዳ የንፋስ ኃይል ማመንጫን ጨምሮ የአይሻ ሦስት የንፋስ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ አራተኛው ነው፡፡
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

