በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የመልካ ዋከና የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ለረጅም ዓመት አስተማማኝ ኃይል እያመረተ እንዲቆይ የጥገና ክፍሉ ሚና ከፍተኛ መሆኑን የጣቢያው የጥገና ክፍል ኃላፊ ገለፁ፡፡
ኃላፊው አቶ መንበሩ ደምሴ እንደገለጹት የጥገና ክፍሉ በራስ አቅም ወቅቱን የጠበቀ ትልልቅ የጥገና ሥራዎችን በማከናወኑ ጣቢያው ላለፉት 37 ዓመታት አስተማማኝ ኃይል በማምረት ላይ ይገኛል፡፡
በጣቢያው ላይ የመልሶ ግንባታ ሥራ ካለመሰራቱ ጋር ተያይዞ በኦፕሬሽንና በጥገና ክፍሉ ላይ ጫና መፍጠሩን የተናገሩት አቶ መንበሩ በማመንጫ ጣቢያው በየቀኑ፣ በየሳምንቱና በየወሩ የቅድመ መከላከል፣ የትንበያ እና የፍተሻ ጥገና ሥራዎች በማከናወን ጣቢያው ዛሬም ድረስ ኃይል ማምረቱ ሳይቋረጥ መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡
የጥገና ሥራዎችን በአግባቡ ለማከናወንም ለባለሙያዎቹ አጫጭር የሥራ ላይ ሥልጠናዎችን እንደሚሰጡና እርስ በእርስ የሚማማሩበት ሥርዓት መዘርጋቱን ጠቁመዋል፡፡
በጣቢያው ከ3 ዓመት በላይ የሠራችው የጥገና ባለሙያ ስናፍቅሽ ጴጥሮስ ተርባይኖች እንዳይቆሙ ዕቃዎች ላይ ማሻሽያ በመስራት ጭምር በራስ አቅም በርካታ የጥገና ሥራዎችን እየሰሩ መሆኑን ተናግራለች፡፡
የጥገናና የኦፕሬሽን ክፍሉ ጥንካሪ ጣቢያው ለረጅም ዓመት ኃይል በአስተማማኝነት እንዲያመርት ማስቻሉንም ጠቁማለች፡፡
በጣቢያው የጥገና ባለሙያ ጥላሁን አጥሌ በበኩሉ የጥገናና የኦፕሬሽን ሥራዎች የጣቢያውን የኃይል አቅርቦት አስተማማኝነት ለመጨመር በሚያስችል መልኩ እየተከናወኑ መሆኑን ገልጿል፡፡
በጣቢያው ከ30 ዓመት በላይ ልምድ ያላቸው የጥገና ሠራተኞች ልምዳቸውን እያካፈሉ ከኦፕሬሽን ክፍሉ ጋር በመናበብ ጣቢያው ችግር ሳይገጥመውና ሳይቆም በርካታ የቅድመ መከላከል የጥገና ሥራዎች እንደሚሰሩ ተናግሯል፡፡
በመልካ ዋከና የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ የኦፕሬሽን ክፍል ኃላፊ አቶ ተክሉ ጎንፋ ክፍሉ በኃይል ማመንጫ ጣቢያው የማዘመን ሥራ ባለመሰራቱና ማንዋል በመሆኑ የኦፕሬሽን ሥራውን ከማዕከል ሆኖ ለመቆጣጠር ፈታኝ እንዳደረገው ተናግረዋል፡፡
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”



